Home ዜና በትግራይ የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች በአፋጣኝ ለአርሶአደሩ እንዲዳረስ አራት የአለምአቀፍ ዩንቨርስቲዎች ተመራማሪዎች...

በትግራይ የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች በአፋጣኝ ለአርሶአደሩ እንዲዳረስ አራት የአለምአቀፍ ዩንቨርስቲዎች ተመራማሪዎች እና ምሁራን ጠየቁ፡፡

684

ዓለምአቀፍ ማሕበረ-ሰብ በትግራይ በወራሪ ሃይሎች የወደሙና የተዘረፉትን ምርጥ ዘርና ማዳበርያን ጨምሮ የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች በአፋጣኝ ለአርሶአደሩ እንዲዳረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ አራት የአለምአቀፍ ዩንቨርስቲዎች ተመራማሪዎች እና ምሁራን ጠየቁ፡፡

ምሁራኑ አሁን ላይ በትግራይ ሰብል የሚዘራበት ወቅት በመሆኑ አርሶአደሩ የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች በማጣት ለሁለተኛ ግዜ መሬቱን ሳይዘራ እንዳያልፈው ድጋፉ በወሳኝነት መልኩ አሁን መሆን አለበት ይህ ካልሆነ ግን ርሃቡ እንዲባባስ እና የሚልዮኖች ህይወትም ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ኢንስቲትዩት ኦፍ ዴቨሎፕመንት ስታድይስ በተባለው ድረገፅ ላይ “ጦርነቱ ባስከተለው ርሃብ እየተሰቃየ ያለው የትግራይ አርሶ አደር አፋጣኝ ድጋፍን ይሻል “ በሚል ርእስ ሓሳባቸውን ያጋሩት የአራት የተለያዩ አለምአቀፍ ዩነቨርስቲዎች ምሁራን እና ተመራማሪዎች ከአስራ ስምንት ወራት በላይ በዘለቀው የትግራይ ጦርነት ሆን ተብሎ ከወደመው እና ከተዘረፈው የትግራይ ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ መሰረተልማቶች መካከል የግብርናው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው ፣ በዚህም  የትግራይ የምግብ ስርዓት ፈርሶ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በሰው ሰራሽ ረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የኖርወይ ዩንቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪ ተክለሃይማኖት ወልደምካኤል፣ የደቡብ ካሮሊና ሜዲካል ዩነቨርስቲ ተመራማሪ ሙልጌታ ገበረእግዛብሄር፣ የኖርዌይ ዩንቨርስቲ የስነ ህይወት ሳይንስ ተመራማሪ መለይ መኮነን እና ፕሮፌሰር ለይላ ማህታ በጋራ ባሰፈሩት ፅሁፍ የትግራይ አርሶአደሮች በበርካታ ምክንያቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል ይላሉ፣ በወራሪ ሐይሎች ሆን ተብሎ በእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች ላይ የተፈፀመው ውድመት እና ዝርፍያ የእርሻ ስራዎችን ለማከናዎን አዳጋች አድርጎታል እንዲሁም ባለፈው ዓመት ወራሪ ሐይሎች በትግራይ ምድር በነበሩበት ወቅት አርሶ አደሩ የእርሻ ስራዎች ዝግጅት እንዳያከናውን በኤርትራ ወታደሮች፣ በፋሽስቱ ቡድን ቅጥረኛ ሰራዊት እንዲሁም በተስፋፊው የአማራ ሃይል ታጣቂዎች በመከልከሉ የግብርናው ዘርፍ ስራዎች እንዲቆሙ ሆኗል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ህዝብ ላይ የተጣለው ከበባ እና ክልከላ አርሶ አደሮቹ የእርሻ ግብአቶች ምርጥ ዘር እና ማዳበርያ እንዳያገኙ ተደርገዋል የወደመው እና የተዘረፈው የእርሻ መሳርያዎች እና ግበአቶችም ለመተካት ተቸግረው ሁለት ተከታታይ የመህር ወቅቶች ሳያመርቱ አልፏቸዋል ሲሉ ምሁራኑ አብራርተዋል፡፡

የትግራይ ጀኖሳይድ ጦርነት ለሶስት አስርት አመታት ለውጦችን ሲያስመዘግብ የነበረው የትግራይ የእርሻ፣ የምግብ እና አካባቢያዊ ዘርፎች እንዳልነበሩ አድርጓቸዋል የሚሉት ምሁራኑ አሁን ላይ ከአለምአቀፍ ማሕበረሰብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እየቀረበ ካለው ሰብአዊ እርዳታ በዘለለ የትግራይ እርሻ ዘርፍ የገጠመውን ቁልፍ ፈተናዎች ትኩረት እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይ በምግባረ ሰናይ እና በልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፉ የነበሩት አለምአቀፍ ተቋማት እጃቸውን አጣምረው እየተመለከቱት ያለውን ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች በረሃብ አፋፍ ያሉበትን የትግራይ ቀውስ ለመፍታት ምሁራኑ መደረግ አለበት ስላሉት የመፍትሄ እርምጃም ለአለም ባንክ፣ ለአለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዩኤስኤድ የመሳሰሉትን አለምአቀፍ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህም በወራሪ ሃይሎች የወደሙና የተዘረፉትን የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች ማለትም ምርጥ ዘርና ማዳበርያ በአፋጣኝ ለአርሶአደሩ እንዲዳረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ የትግራይ አርሶአደር ከዚህ ቀደም ለእርሻ ክንውን ይጠቀምባቸው የነበሩት በሬዎች በወራሪ ሃይሎች መዘረፋቸውን ተከትሎ አሁን ላይ በሬዎችን ለመተካት የሚያስችል ኢኮኖሚኒያዊ አቅም ስለሌላቸው የእርሻ ስራዎች ለማከናዎን የሚያግዙ ቀላል መሳርያዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ የእርሻ ምርት እና ምርታማነት በማጎልበት ረገድ የጎላ ድርሻ ያላቸው የእርሻ ምርምር ተቋማት፣ የአርሶአደሮች ማሰልጠኛ ማእከላት እንዲሁም የግብርና ዘርፉ መሰረተልማቶች መልሶ ማቋቋም እና ማጠናከር ላይ ድጋፍ እንዲደረግ፣ የግብርና ዘርፍ እንዲሁም አጠቃላይ የትግራይ ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ወደነበረበት ለመመለስ ፋሽስቱ የአብይ ቡድን ባንክ፣ መብራት እና ስልክ የመሳሰሉት መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲከፍታቸው የአለም አቀፍ ማሕበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ምሁራኑ ጠይቀዋል፡፡  

ምሁራኑ በፅሁፋቸው ማጠቃለያ አሁን ላይ በትግራይ ሰብል የሚዘራበት ወቅት በመሆኑ የእርሻ መሳርያዎች እና ግብአቶች በማጣት ለሁለተኛ ግዜ መሬቱን ሳይዘራ እንዳያልፈው ድጋፉ በወሳኝነት መልኩ አሁን መሆን አለበት ይህ ካልሆነ ግን ርሃቡ እንዲባባስ እና የሚልዮኖች ህይወትም ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣል ሲሉ ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡        

ዳርይስማው ሃይሉ