Home ዜና በትግራይ ተወላጆች ላይ  ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመግታት የትግራይ ምሁራንና ባለሙያዎች ማህበረሰብ...

በትግራይ ተወላጆች ላይ  ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመግታት የትግራይ ምሁራንና ባለሙያዎች ማህበረሰብ እየሰራ ነው

1176
0

ተስፋፊው የአማራ ሐይሎች በትግራይ ህዝብ ላይ የጥላቻ ንግግር በመስበክና ጀኖሳይድ በማበረታታት አሉታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አለም አቀፍ የትግራይ ምሁራንና ባለሙያዎች ማህበረሰብ እንዳሳሰበው ገለፀ፡፡

CNN ባደረገው ምርመራ እንዳረጋገጠው ፌስቡክ በትግራይ ህዝብ ላይ ግድያ እንዲፈፀም የሚቀሰቅሱ ይዘቶች ሲወጡ አይቶ እንዳላየ ማለፉ አሳፋሪ ተግባር መፈፀሙን ተገልጿል፡፡

አለም-አቀፍ የትግራይ ምሁራንና ባለሙያዎች ማህበረ-ሰብ GSTS  ቀድሞ ፌስ ቡክ ተብሎ ይጠራ ለነበረውና አሁን በአዲስ አደረጃጀት ለተሰየመው  ሜታ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግና ሌሎች የሜታ የስራ ሃላፊዎች በፃፈው ደብዳቤ ተቋሙ የአማራ አክራሪዎች በትግራይ  ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግርና የተቀነባበረ ጀኖሳይድ እንዲፈፀም የሚያነሳሱ መልእክቶችን እያስተናገደ በመሆኑ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጻል፡፡

በትግራይ ህዝብ ላይ የጥላቻ ንግግርና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መልእክቶች ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በተቋሙ ፈስቡክ የመገናኛ  አውታር አማካይነት ለህዝብ እንዲደርስ በመፍቀዱ ሜታ  እየቀጠለ ላለው ጀኖሳይድ አስተዋጸኦ እያደረገ ነው ብሏል አለም አቀፉ የትግራይ ምሁራንና ባለሙያዎች ማህበረ-ሰብ   GSTS  በደብዳቤው፡፡

GSTS  በሚያሳስቡት ጉዳዮች ላይ ከሜታ ተወካዮች  ጋር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካሄድ የጠየቀ ሲሆን በዚሁ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥፋት ዘመቻ ትኩረት የሚያደርግ አንድ ግብረሃይል  እንዲቋቋምና ችግሩን ለመቅረፍ እንዲቻል ከትግራይ የሰብአዊ መብት ተማጓቾችና ሲቪክ ማህበራት ጋር ምክክር እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ከትግራይ ጦርነት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ጉዳዮችና  በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረው ጀኖሳይድ ይዘቶችን በተመለከተ የሜታ  የኦንላይን መልእክት  መስተንግዶ መድረክ  ደህንነት  እንዲሻሻል የጠየቀው ማህበረሰቡ ቋንቋው በማይችሉ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ አውዱንና ዳፋውን በማይገነዘቡ ሰዎች መስተናገድ እንደሌለበት አሳስቧል፡፡

ሜታ በመገናኛ አውታሩ የሚተላለፉ ይዘቶች በምንያህል መጠንና አግባብ  የጀኖሳይድ ወንጀልን እንዲባበስ ማድረጋቸው አስቸኳይ የማጣራት ስራ እንዲጀምርም GSTS  ጠይቋል፡፡

አክራሪና ተስፋፊው የአማራ  ሃይል ፌስቡክን በመጠቀም በትግራዋይነታቸው ብቻ  ያተኮረ የጅምላ ግድያዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ መፈፀማቸው  ያስታወሰው የ GSTS  ደብዳቤ የCNNን ምርመራ ውጤትን ጠቅሶ እንዳለው ሜታ በፌስቡክ የመገናኛ አውታሩ በትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ እንዲፈፀም የሚቀሰቅሱ መልእክቶች መለጠፋቸው ፌስቡክ ራሱ እያወቀ እርምጃ አለመውሰዱንና በችልታ ማለፉን አሳፋሪ ነው፡፡

በፌስቡክ በሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች ሳቢያ  በአማራ ክልልና በሌሎች ኢትዮጵያ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሰለባዎች መሆናቸው ያመለከተው GSTS  ከጥላቻ ንግግሩ ጎን ለጎን  የጉዳቱ ሰለባ  የትግራይ ተወላጆች ፎቶግራፍ  አብሮ ይሰራጭ እንደነበረ በማመልከት በዚሁ በትግራዋይነታቸው ብቻ  በአማራ ክልል ይኖሩ በነበሩ 10 የትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ መፈጸሙ አስታውሷል፡፡ የአንዱ የጉዳቱ ሰለባ ወገን ቤተሰብ  ለግድያው  ሰበብ የሆነው  በማህበራዊ መገናኛ  ብዙሃን ይሰራጩ የነበሩ የጥላቻ መልእክቶችና ንግግሮች መሆናቸው መናገራቸው በዚሁ የማህበረ-ሰቡ ደብዳቤ ተጠቅሷል፡፡

የመብት ተማጓች የትግራይ ተወላጆች  የአክራሪና ፅንፈኛ የአማራ ሃይሎች ግጭትን የሚቀሰቅሱ መልእክቶችና ንግግሮችን በተመለከተ ሳይታክቱ ረፖርት ያቀርቡ እንደነበረ ያስታወሰው ደብዳቤው በአብዛኛው በተሰራጩ መልእክቶች ምንም የተጨበጠ እርምጃ አለመወሰዱ አስታውቋል፡፡

የዚህ ችግር  ምክንያት ፌስቡክ ሆነ ብሎ እርምጃ ያለመውሰድ ወይም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚለጠፉትና የሚነገሩትን  መልእክቶችን የሚቆጣጠር  አካል አለመኖር ወይም የተዛባ አመለካከትና ከአውድ ውጭ  የሚተላለፉ መልእክቶችን የሚያስተናግዱ አካለት ድንቁርና  ወይም የነዚህ ሁሉ  ምክንያቶች ድምር ውጤት ሊሆን እንደሚችል እምነቱን አስቀምጧል GSTS  ፡፡

በዚህ የተነሳ ሜታ  የፌስቡክ የመገናኛ  አውታሩን እንደመሳሪያ ለሚጠቀሙ አካለት ክፍት በማድረግ በትግራይ ተወላጆች ላይ የጀኖሳይድ ወንጀል እንዲቀጥል መፍቀዱ ያሳሰበው GSTS  የትግራይ ተወላጆችይህን የሜታ እርምጃ ላለመውሰድ ያሳየው ዳተኝነት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው  ይጠብቃሉ ብሏል፡፡

GSTS  ይህንኑ በትግራይ ተወላጆች ላይ  ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመግታት ሜታ ለሚያደርገው ጥረት  ትብብሩን እንደማይነፍገው አስታውቋል፡፡

Previous articleትክክለኛና ሃቀኛ ብሄራዊ እርቅ ከመጣ ለመደገፍና ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸው ፕሮፌሰር  መረራ  ጉዲና ተናገሩ፡፡
Next articleኢትዮጵያ በትግራይ ለተፈጸመው ጀኖሳይድ ማስረጃ የማጥፋት ዘመቻ