Home ዜና የአብይ ቡድን ለማካሄድ ያቀደውን ሃገራዊ ምክክር ገና ከጅምሩ ሞቷል ሲል የአፍሪካን አርጉመንትስ...

የአብይ ቡድን ለማካሄድ ያቀደውን ሃገራዊ ምክክር ገና ከጅምሩ ሞቷል ሲል የአፍሪካን አርጉመንትስ ገለፀ፡፡

የአብይ ቡድን ዘላቂ ሰላም ያመጣል በሚል የተጭበረበረ እቅድ ያቋቋመውን ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን አካታችና ህጋዊነት የተከተለ ባለመሆኑ ከጥንስሱ እንዲመክን ምክንያት መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስታወቀው፡፡ የአፍሪካን አርጉመንትስ ድረ ገፅ በአብይ ቡድን የተቋቋመው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽንን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ባሰፈረው ሰፊ ፅሁፍ ላይ፣ የአብይ ቡድን 11 አባላት ያሉት ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ #ሰላም ለማምጣት ያስችላሉ በማለት ቢሰነባብትም ቅሉ፣ እቅዱ ግን እውነተኛ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አያስችልም ብሏል፡፡ የአብይ የብልጽግና ፓርቲ ከሚደግፉ ሦስት የፖለቲካ ፖርቲዎች በስተቀር ሌሎችን ሳያካትት የተቋቋመው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ያለው ድረ ገፁ፣ የአብይ ዓላማ ከጅምሩ ስልጣንን ጠቅልሎ ለማያዝ ካለው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ ሂደት ነው ሲል አስታውሷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 50 ተፎካካሪ ፖርቲዎች መካከል የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ድጋፍ አግኝቶ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፣ ማን በምክክር መድረኩ ይሳተፍ፣ ሃገራዊ ጉዳዮች እንዴት ይደራጁ የሚሉ ጥያቄዎችን ሳይመልስ ከመቋቋሙም በተጨማሪ ህጋዊነት፣ ግልጽነትና ታአማንነት የጎደለው መሆኑን አመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑን እንዲመሩ የተመረጡ 11 አባላትም በምን መመዘኛ እንደተመረጡ ግልጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሁሉንም አባላት የአብይ ደጋፊዎች መሆናቸውን ያስታወሰው ድረ ገጹ፣ ኮሚሽኑ የብልጽግና ፓርቲ የውስጥ ችግር ብቻ ለመፍታት የተቋቋመ እንጂ በሃገሪቱ የሚታዩ መሰረታዊ የፖሊቲካዊ ችግሮችን የሚፈቱበት ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥም አይደለም ሲልም ነው ድረ ገጹ ትችቱን ያስቀመጠው፡፡ ከጥንስሱ በበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት ያጣው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በተለይ በትግራይ ህዝብ ዘንድ መዳረሻውን ሳይደርስ ከጥንስሱ ስለመውደቁ ነው ድረ ገጹ የገለጸው፡፡ ምክንያቱም ይላል ድረ ገጹ፣ ሃገራዊ የምክክር መድረኩ ይካሄዳል ተብሎ የታቀደው በትግራይ ህዝብ ላይ የተከፈተውን ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት እና መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች የሆኑ የኤሌክትሪክ ፣የኢንቴርኔት እና የባንክ አገልግሎቶች በተቋረጠበት ጊዜ ላይ መሆኑን በማስረጃነት አስቀምጧል፡፡ ከትግራይ ህዝብ በተጨማሪም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦጋዴን ነጻነት ግንባር በግልጽ ተቋውመውታል ያለው አፍሪካን አርጉመንትስ፣ የተቋቋመው ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሺህ የሚቆጠሩ አባሎቻቸው በታሰሩበት ወቅት እና አካታችነት በጎደለው መልኩ የተከናወነ በመሆኑም ነው ብሏል፡፡ በተለይ ኮሚሽኑ ከሁሉም በላይ ገለልተኛነት፣ ህጋዊነት፣ ግልጽኝነት፣ ፍትሃዊነት፣አካታችነት የጎደለው እና ተጠያቂነት የለውም ሲሉም ነው ተቋማዊ ፓርቲዎቹ የተቋወሙት፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ የአብይ ቡድን አሸባሪዎች ናቸው በማለት የፈረጃቸው የህወሓትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጭምር በመድረኩ እንዲሳተፉ መጋበዝ በተገባው ነበር ሲሉም ነው ድረ ገጹ ሃሳቡን ያስቀመጠው፡፡ በአጠቃላይ የአብይ ቡድን ያቋቋመው ኮሚሽን የፈለገው ስልጣን በራሱ ጠቅልሎ ለመያዝ እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማጭበርበር ካለው ፍላጎት ነው ያለው የአፍሪካን አጉርመንትስ ሐተታ፣ መንገዱ ስለማያዋጣው አካታች፣ ህጋዊነትና ግልጽኝነት ያሟላ ኮሚሽን እንዲኖር መፈቅድ አለበት ሲልም አሳስበዋል፡፡ በእርግጠኝነት ይህን ተግባራዊ ከተደረገ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያለጥርጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ የታቀደው ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ እውን ይሆናል ሲልም ነው ድረ ገጹ ሃሳቡን የቋጨው፡፡ በአማረ ኢታይ

1016
0
Previous articleየዛላንበሳ እናቶች ሰቆቃ
Next articleየኤስ 3199 ረቂቅ ህግ ፀደቀ