Home ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር...

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

300
0

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሀይልን መሰረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ ተሳትፏል በሚል ምክንያት የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ መወሰኑን ተከትሎ፤ የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ሥም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እንዲሁም የፓርቲው ንብረት ፓርቲው ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሽፈኛ እንዲውል ቀሪው ገንዝብና ንብረት ደግሞ ለሰነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውል ሲል ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም መወሰኑ ይታወቃል

። ሆኖም ህወሓት፤ ጦርነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሕዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ ከኢፌዴሪ መንግስት ጋር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግጭትን የማቆም ስምምነት ፈርመዋል። በዚሁ ስምምነት መሰረትም ህወሓት በሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ጥያቄዎቹን ለመመለስ ወደሚይስችለው ምዕራፍ ገበቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በዚህም ምክንያት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ከአሸባሪነት መዝገብ ተሰርዞ በትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር ገብቶ መሪ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነውን ህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሕግም በፖልቲካም ተቀባይነት የለውም።

ምክንያቱም ውሳኔው የሰላም ስምምነቱ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ህወሓትን ወክለው በትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር እየተሳተፉ ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች እውቅናን በመንፈግ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ህልውና አደጋ ላይ ይሚጥል እንዲሁም አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገራችን የተጀመረውን ተስፋ ሰጭ የሰላም መንገድ ለመደገፍ ሕግን በአወንታዊ የትርጉም ስርዓት ከመረዳት ይልቅ፤ ቴክኒካዊ በሆነ አረዳድ ሰላማዊ ፖለቲካዊ መግባባትን ማደናቀፍ አይኖርብትም።

ይህ አካሄድ እንደ ህወሓት ወደ ሰላማዊ ትግል ለመመለስ ለሚዘጋጁ ሀይሎችም ተስፋ የሚያስቆርጥ ተግባር ነው።ስለሆነም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ የትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል እና አጠቃላይ የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፍ ተግባር በመሆኑ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ጥሪያችንን እናቀርባለን። የትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር

ግንቦት 08 ቀን 2015 ዓ.ምመቐለ

Previous articleበብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ የተላለፈዉ ዉሳኔ አስመልክቶ በህወሓት የተሰጠ መግለጫ
Next articleበመቐለ ከተማ ከ50 እስከ 60 ሺህ ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ ሪልስቴት ለመገንባት ወጋገን ባንክ ከሱር ኮንስትራክሽን ጋር ውል ተፈራረመ።