Home ዜና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የልብ ወዳጅ፤ ዐቢይ አሕመድ አሊ!

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የልብ ወዳጅ፤ ዐቢይ አሕመድ አሊ!

2628
0

(በብርሃኑ ድረስ ከባሕርዳር)

ዐቢይ አሕመድ የተባለ ሰው አራት ኪሎ ከመግባቱ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥታትና ነገሥታት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ላይ ቁማር ተጫውተው አያውቁም፡፡የውስጥ ችግሮች ቢኖሩባቸው እንኳን ቅድሚያ የአገራቸውን ግዛት የወረረን የትኛውንም ሃይል ለመምታት ወደ ጠረፍ ይዘምታሉ፡፡አጼ ቴዎድሮስ በውስጥ ከሕዝቡም ከቤተክህነቱም የነበረባቸውን ችግር ትተው መቅደላ ሄደው ለአገር ሉዓላዊነት ሞተዋል፤አጼ ዮሃንስ በውስጥ ንግሥናቸውን የሚገዳደር ተቃዋሚ ቢያይልባቸውም መተማ ላይ ሄደው የሞቱት ለአገር ክብር ነው፤አጼ ምኒልክ ‹‹ውሾች እርስበርስ እየተጣሉ ጅብ ቢመጣባቸው የራሳቸውን ፀብ ወደ ጎን ብለው ጅቡን ለመከላከል እንደሚተባበሩት እኛም የውጪ ጠላቶቻችንን ለመግታት የውስጥ ችግራችንን እንግታ›› ብለው አድዋ ዘምተዋል፡፡

አጼ ኃይለሥላሴ እንደ ታከለ ወልደሃዋርያት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን ትተው ማይጨው ላይ የዘመቱት፣እንደ ጀብሃ ያሉ ነፍጥ አንሺ ተፋላሚዎቻቸውን አቆይተው የሶማሊያን ወረራ ለመግታት (በ1959) ጦራቸውን ወደ ኦጋዴን የላኩት ከሥልጣን አገር ይቀድማል ብለው ነው፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም የሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ ሲዘምቱ፣ ሻዕቢያ፣ጀብሐ፣ ኢሕአፓ፣ ሕወሓት፣ኢዲዩ፣ ኦነግ ወዘተ የተባሉ ተቃዋሚዎቻቸው የከፈቱባቸውን ጦርነት ወደ ጎን ብለው ከውስጥ ፀብ ይልቅ የውጪ ወረራ አዋራጅና አሳፋሪ ነው ብለው ነው፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ የሻዕቢያን ወረራ በባድመ፣የአልሸባብን ጂሃድ በሶማሊያ በኩል ለመመከት ሲዘምቱ ተቃዋሚዎቻቸው በአስመራም፣በካይሮም እየተደገፉ በኢትዮጵያ በሕቡዕ በዳርድንበር ደግሞ ከጠላት ጋር ተሰልፈው እየተዋጓቸው ነው፡፡

ይህንን አኩሪ ታሪክ ያከሸፈውና ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሁሉ ኢትዮጵያን ገባር ያደረጋት ዐቢይ አሕመድ አሊ የተባለው የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡

በተለምዶ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚባሉት የአረብ አገራት፣ግብጽ፣ቱርክ፣ሶማሊያ፣ኤርትራና ሱዳን ናቸው፡፡ከነዚህ ሁሉ አገራት ጋር ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተባበረ ብቸኛ የኢትዮጵያ መሪ ዐቢይ አሕመድ ነው ሲባል ተራ ውንጀላ ሳይሆን በቂ ማስረጃ የሚቀርብበት ነው፡፡

አልሸባብ በታሪኩ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ገብቶ የፈፀመው አንዳች ጥቃት ኖሮ ባያውቅም ዐቢይና የጅግጅጋ ምስሌነው ባደረጉት ትብብር ከ150 ኪሎሜትር በላይ ዘልቆ ገብቶ ጥቃት ፈጽሟል፤አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እየተጎማለለ ነው፡፡መንግሥቱ ሃይለማርያምና አጼ ሃይለሥላሴ እንዲህ ያለ መዋረድ እንዳይመጣ ነው የውስጥ ጉዳያቸውን ገታ አድርገው በግብጽ የሚደገፈውን የሶማሊያ ወረራ ለመፋለም የዘመቱት፡፡የአሁኑ ሰባተኛ ንጉሥ ግን የራሱን ሕዝብ ለማጫረስና ለመጨረስ እጁ የገባውን ቦንብ ሁሉ ይወረውራል፡፡

የሱዳን መንግሥት በኢሕአዴግ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የተካለለበትን መሬት እንዲወስድ አዲስ አበባ ድረስ ጠርቶ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም ፈቃድ የሰጠው ዐቢይ መሆኑን እራሳቸው ጀኔራል አል ቡርሃን በመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡ብርሃኑ ጁላ የተባለው የዐቢይ ፀረ-ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስፈፃሚ ደግሞ የኢትዮጵያን ግዛት ለማስመለስ እንደማይዋጋ ገልፆ፣የትግራይ ሕዝብ መራብና መጠማት ላይ ግን ተግቶ እንደሚሠራ በአደባባይ ተናግሯል፡፡

የአረብ አገራትን ‹‹ኢትዮጵያ ጠላት የላትም፤አረቦቹን ጠላት አድርገው የኖሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥታት ስህተተኛ ናቸው›› ብሎ በመፅሐፍ ጭምር የፃፈውና ይህንንም በንግግር ያብራራው ዐቢይ አሕመድ ነው፡፡ዛሬም ከእነዚሁ አገራት በሚያገኘውና ሃይማኖታዊ አጀንዳ ባዘለው እርዳታ የአገሩን ሕዝብ እየጨፈጨፈ ነው፡፡

‹ወላሂ ወላሂ አንቺንስ አልጎዳሽም› ብሎ ቃለ መሀላ የፈፀመላት፣የሕዳሴ ግድብን ብቻ ሳይሆን ግድቡን የጀመሩትን ሃይሎች ሁሉ አሳድድልሻለሁ ብሎ ቃል የገባላት ግብጽ ደግሞ ሌላኛዋ የዐቢይ ሸሪክ ነች፡፡6450 እንዲያመነጭ የተጀመረን ግድብ 1300 ሜጋ ዋቱን በመቀነስ ወደ 5150 ያወረደ፣የዓለም ባንክንና አሜሪካን በአደራዳሪነት እንዲገቡ ያደረገ፣አሁን ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሸምጋይነት እንድትገባ የፈቀደ፣ዓመት 9 በመቶ ይገነባ የነበርን ግድብ አሁን ወደ ሶስት በመቶ ብቻ እንዲሆን ያወረደ፣የውሃውን የመያዝ አቅም እንዲቀንስ ያደረገ የግብጽ ባለውለታ ነው፡፡የግድቡን መሐንዲስ ከመግደል (?) ጀምሮ ግድቡን ያስጀመሩትን ሃይሎች እስከማሰር የደረሰው የዐቢይ ውለታ በካይሮ የሚረሳ ሊሆን አይችልም፡፡

 ዐቢይ ግን ሕወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እርዳታ እየተሰጠው ነው ይላል፡፡ይህ ማለት ግብፆች የሕዳሴ ግድብን አስጀምሮ ጉድ የሠራቸውን ሕወሓትን መልሰው ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ይፈልጋሉ ማለት ነው፡፡ወይም በአጼ ዮሃንስም በራስ አሉላም ድባቅ የመታቸውን የትግራይን ሕዝብ ከዐቢይ የበለጠ ይወዱታል ማለት ነው፡፡

እውነታው አገር እንዲፈርስ ዐቢይ አምስት መቶ ሺህ ዶላር ከግብጽ ተቀብለናል ብለው በአደባባይ ከሚናገሩት የግንቦት ሰባትና የሻዕቢያ ሰዎች ጋር የጀመረው ፀረ ኢትዮጵያ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው፡፡

የኤርትራው መንግሥት ከ1950ዎቹ የጫካ ዘመኑ ጀምሮ ላለፉት 60 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከእነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሲሠራና የኢትዮጵያ መንግሥታትን ሲወጋ የኖረ ነው፡፡ዛሬ ግን ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቡድን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን እያፈረሰ ነው፡፡

እስከዛሬ በነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቱርኮችም ሆነ አረቦቸና ግብጽ፣ሱዳንም ሆነ የኤርትራ መንግሥት የሚያስታጥቁት የመንግሥትን ተቃዋሚዎች ነበር፡፡በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግን አሁን እነዚህ ሁሉ ሃይሎች እያስታጠቁና እያገዙ ያሉት መንግሥትን ነው፡፡ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡እስከዛሬ አገሪቱን ለማፍረስ የተሻለው አቅጣጫ በተቃዋሚዎቹ በኩል ይገኛል ብለው ስላሰቡ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ አለያም በኃይለሥላሴ ዘመን የመንግሥት ተፋላሚዎች የውጪ እርዳታ ያገኙ ነበር፡፡

አሁን ግን እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ዐቢይን ለመደገፍ የእየተረባረቡ ነው፡፡ምክንያቱም አገሪቱን ለማፍረስ ትክክለኛውን መዶሻ የጨበጠ ሰው አራት ኪሎ እንደገባ አውቀዋል፡፡እንዲህ ያለ የሎሌነት ተግባር ያለው ሰው ነው እንግዲህ ሌሎችን በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪነት የሚከሰው፡፡ስሙን ለሰው አወረሰው የሚሉት ተረት ይሄ ነው፡፡የዐቢይ አሕመድ ተግባር እርሱን ለደገፉ፣በእርሱ ዙሪያ ተሰልፈው ለሰሩ፣በእርሱ ዘመን በየትኛውም መንገድ ተሹዋሚ ሆነው ለሰሩ ሁሉ አሸማቃቂ ብቻ ሳይሆን በአገር ክህደት የሚያስቀጣቸውም ነው፡፡ወደፊት ይህንን ዝም ብሎ የሚያልፍ ትውልድ ካለ እርሱም ሌላኛው የኢትዮጵያ ጠላት መሆን አለበት፡፡

Previous articleበመቐለ  መዋእለ ህፃናት ከተካሄደው የአየር ድብደባ በህይወት የተረፉት ህፃናት በከፍተኛ የአእምሮ መረበሽ ውስጥ እንደሚገኙ ተገለፀ።
Next articleሰበር የድል ዜና – መስከረም 3, 2015 ዓ/ም