Home ዜና የኤርትራውያን ስደተኞች ጥቃት በአማራ ክልል

የኤርትራውያን ስደተኞች ጥቃት በአማራ ክልል

607
0

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ በሚገኘው የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ በታጣቂዎች ጥቃት እንደደረሰበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለፀ።ቅዳሜ ምሽት በታጣቂዎቹ በተፈፀመው ጥቃት ስምንት ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውንም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በምስራቅ አፍሪካ እና በግሬት ሌክስ የስደተኞች ተጠሪ ቃል አቀባይ ፌይዝ ኪሲንጋ ቅዳሜ ምሽት ታጣቂዎቹ አዲስ በተከፈተው መጠለያ በመግባት በፈፀሙት ጥቃት ስምንት ስደተኞች በጥይት እንደተሞቱ እና እንደቆሰሉ ለBBC ገልፀዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ሕክምና እንደተደረገላቸው እና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል።ታጣቂዎቹ በቁጥር ስድስት እንደነበሩ የገለፁት ኃላፊዋ ዓላማቸው ምን እንደነበር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በትግራይ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች የተሻለ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ለማዘዋወር በሚል ነበር ይህንን መጠለያ ጣብያ ያቋቋመው።ከዚህ ቀደም በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ ወደተገነባው አዲስ ጣቢያ እንደሚዘዋወሩ ተቋሙ ገልፆ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እና የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ባለሥልጣናት ጥቃቱ በደረሰ ማግሥት በጋራ ወደ ማቆያው መሄዳቸውን እና የስደተኞቹን ደህንነት በተመለከተ ከመንግሥት ጋር መነጋገራቸውን አክለው ገልፀዋል። ጥቃቱን የፈፀሙ ታጣቂዎች ማንነት እስካሁን ድረስ ያልታወቀ ሲሆን የአካባቢው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ጨምረው አስረድተዋል።

ቃል አቀባይዋ ፌይዝ ኪሲንጋ በትግራይ ማይጸብሪ በሚገኙት ሁለት የስደተኞች መጠለያ 22 ሺህ 500 ስደተኞች መኖራቸውን ይናገራሉ። በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በተመለከተ ሲናገሩም “በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። ሁኔታው ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መጥቷል” ብለዋል። በማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ካምፖቹ ውስጥ የንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የምግብ እጥረት መኖሩን የተጠየቁት ኃላፊዋ፣ የካቲት ወር መጨረሻ ከአካባቢው ባለስልጣናት በመነጋገር 290 ሜትሪክ ቶን እህል ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወደ ሽረ እንዲሄድ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።

ስደተኞቹ በጦርነት ምክንያት ለተለያዩ ጥቃቶች በመጋለጣቸው የደህንነት ዋስትና ወዳለው አካባቢ እንዲዘዋወሩ ሲጠይቁ እንደነበርም ተናግረዋል።ስደተኞቹን ወደ ሌላ ስፍራ ለማጓጓዝ ደህንነቱ የተጠበቀ መስመር ሊኖር እንደሚገባ የሚናገሩት ኃላፊዋ፣ “ስደተኞቹ የሚገኙበት አካባቢ ደህንነቱ የተጠበቀ ስላልሆነ ወደሌላ ቦታ ማዘዋወር አልቻልንም፤ ስደተኞቹን ለማሸገገር ደህንነቱ የተጠበቀ መስመር እንዲኖር ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል። ጦርነቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት ከመቀስቀሱ በፊት 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይ በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያ ጣብያዎች ማለትም በዓዲ ሐሩሽ፣ ማይ ዓይኒ፣ ሽመልባ እና ሕጻጽ ይኖሩ ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ለስደተኞቹ ጥበቃ የሚሰጣቸው አካል ስላልነበረ ከተዋጊ ኃይሎች በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የሞትና የመቁሰል አደጋ እንዲሁም የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው የሰብአዊ ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቁመዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል በኤርትራ ወታደሮች በግድ ወደ ኤርትራ የተወሰዱ መኖራቸውን በሪፖርቶቹ ላይ አመልክቷል። በትግራይ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ከ21 ሺህ በላይ ስደተኞች ሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ካምፖች የነበሩ ስደተኞች የመገደል፣ ታፍኖ የመወሰድና መበታተን አደጋ እንደገጠማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርቶች ይገልጻሉ።

ኤርትራውያኑ የአገራቸውን አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት እና አፋኝ አገዛዝን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር ይሸሻሉ። ፋሽስቱ ቡድን በትግራይ ያወጀውን ጦርነት ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከፍሎች መሸሻቸውንና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይነገራል ሲል BBCዘግቧል።

በዳርይስማው ሃይሉ

Previous articleሰብአዊ መብት ተማጔቾች የምርመራ ሪፖርት አሳማኝ ነገር የያዘ መሆኑ ምሁራን እየገለፁት ይገኛሉ፡፡
Next articleየአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የዓለም ባንክ ያፀደቀውን የ300 ሚሊዮን ዶላር ጊዜው እንዳልሆነ አስገንዝቧል፡፡