Home ዜና S3199 በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የቀረበ ረቂቅ ሕግ በከፍተኛ ድምፅ ፀደቀ፡፡

S3199 በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የቀረበ ረቂቅ ሕግ በከፍተኛ ድምፅ ፀደቀ፡፡

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ S3199 የተሰኘው ረቂቅ ህግ ማፅደቁ በትግራይ እንደጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ የዋሉ አሰቃቂ ግድያዎች ፆታዊ ጥቃቶች የእርዳታ እገዳዎች ለማስቆም እርምጃ ለመወሰድ የሚያስችል እንደሆነ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሮበርት ሜንዴዝ አስታወቁ፡፡ ሊቀ መንበሩ ይህን የገለፁት የሃገሪቱ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የቀረበ ረቂቅ ሕግ S3199 በከፍተኛ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ነው፤ ረቂቅ ህጉ በሃገሪቱ ተወካዮች ም/ቤትና ፕሬዝዳንት ሲፀደቅ የሃገሪቱ ህግ ሆኖ ይፀናል፡፡ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት የወጣ ድንጋጌ ወይም 'The Ethiopia Peace and Democracy Promotion Act' በሚል ያረቀቀውንና S3199 የተሰኘውን ይህን ህግ በትናንትናው እለት በኮሚቴው ፀድቆ ለሕግ መወሰኛው ምክርቤት ተመርቷል። በሁለቱምፓርቲዎች አባላት በከፍተኛ ድምፅ ያለፈው ይህ ረቂቅ ሕግ አሜሪካ ለአብይ መንግሥት የምትሰጠውን የፀጥታ ድጋፍ ከማገድ ጀምሮ በተጨማሪ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማቆም የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ፣ ከጦርነቱ የሚያተርፉ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲባባስበ ገንዘብ እንዲሁም በቀጥታ የተሳተፉ አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ነው። ረቂቅ ሕጉ ከቀረበበት ከወራት በፊት የነበረው የትግራይ ጀኖሳይድ ጦርነት መልክ መቀየሩን የተናገሩት የምክርቤቱ አባል ጂም ሪሽ፣ በዋነኝነት መሠረታዊ ጉዳዮቹ ግን ተመሳሳይ መሆናቸውን መናገራቸውን የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል። ረቂቅ ሕጉ የጦርነቱተሳታፊ አካላት ለፈጸሟቸው መጠነ ሰፊና አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ጥሰቶች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም አስምረውበታል ሴኔተሩ። በተጨማሪም በዚህ ጦርነት ጣልቃ የገቡ የውጭ አገራት ሚናም እትኩሮት እንደሚሰጠው አውስተዋል። ባለፈው ሳምንት በአብይ መንግሥት የታወጀውን ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ጊዚያዊ የግጭት ማቆም ጥሩ እምርታ ነው ያሉት የምክርቤቱ አባል ነገርግን አንድም የሰብዓዊ እርዳታ ለትግራይ ህዝብ አለመቅረቡና ቅንጣት እርምጃ አልተወሰደም ብለዋል። "ይህ ረቂቅ ሕግ የህግ መወሰኛ ም/ቤቱ መጠየቅ ያለባቸውን አካላትን በተመለከተና ግጭቱን በማስቆም ረገድ ጠንከር ያለ ለመልዕክት ያስተላልፋል" ማለታቸውም መግለጫው አትቷል። በትግራይ ህዝብ ላይ የታወጀው ጦርነት ያለጥርጥር #ጀኖሳይድ ጦርነት መሆኑን እምነታቸውን በተደጋጋሚ የገለፁት የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ሮበርት ሜኔንዴዝ በበኩላቸው ረቂቅ ሕጉ በከፍተኛ ድምፅ በማለፉ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ከዳኝነት ሂደት ውጭ የተደረጉ ግድያዎች፣ የጅምላ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች፣ አስገድዶ የማፈናቀል ተግባራትን እና የሰብዓዊ እርዳታን ክልከላ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ የምንናገርበት ብቻ ሳይሆን እነዚህን አሰቃቂ ድርጊቶች ለማስቆም እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ ነው" ብለዋል። ሴናተር ሜኔንዴዝ እንዳሉት "ድርጊቶቹ የጦር ወንጀሎች፣ በሰው ልጅ ፍጡር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ወይም የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመሆናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ወክለው ኢትዮጵያ መጥተው ከዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የምክር ቤቱ አባል ክሪስ ኩን በበኩላቸው፤ ከዚህ ጉብኝት በኋላ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ግጭት የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብዓዊ ምላሽ የሚያጠናክረውን ይህንን ረቂቅ ሕግ ማስተዋወቃቀቸውን ገልጸዋል። በቅርብ ቀናት ውስጥ የተደረገው የግጭት ማቆም ውሳኔ እና የተሻሻለ ሰብዓዊ አገልግሎት አቅርቦትን በተመለከተ የተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች እንደ በጎ ማየታቸውን ቢጠቅሱም "የግጭቱ ተሳታፊዎች ከቃላት ይልቅ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል። አያይዘው ረቂቅ ህጉ ለዚህ ጥረት ጠቃሚ መሳሪያ ነው" ማለታቸው በመግለጫው ሰፍሯል። በያዝነው ዓመት በፈንጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የቀረበው ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለመደገፍ የአሜሪካ አስተዳደር ዲፕሎማሲያዊ፣ ልማታዊ እና ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅና ይህንንም ሂደት እያደናቀፉ ያሉ አካላት ላይ አስተዳደሩ ማዕቀብ የሚጥልበትን ማዕቀፍ ለመፍጠር ማለሙንም አስታውቃለች። ረቂቅ ሕጉ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን በሴኔቱ ካፀደቀ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይቀርባል፣ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎት ካለፈ በኋላ ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ ፊርማቸውን ካኖሩበት በኋላ ሕግ ሆኖ ተግባራዊ ይሆናል። በተመሳሳይ ሌላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የተመለከተ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መተዋወቁ ይታወሳል። ይህ ረቂቅ ሕግ HR6600 የሚባል ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከጀኖሳይዱ ጦርነቱ ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶቦች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል። የአብይ መንግሥት አጥብቆ የተቃወማቸው እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በፕሬዝዳንት ባይደን ከጸደቁ በኋላ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ትጥላለች። በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም HR6600 ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመከረበት ሲሆን ረቂቅ ሕጉ ለምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ፍትሕ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለጦር ኃይል አገልግሎቶች መርቷል። ይህ ረቂቅ ሕግ ህግ ሆኖ ሲፀድቅ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር መሳሪያ ሽያጭ አታከናውንም። በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶችም ድጋፍ አታደርግም። እንደ HR6600 ሁሉ S3199 ረቂቅ ሕግ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃልና። ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ትጠቀማለች ይላል ረቂቅ ሕጉ። እነዚህ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ እና ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚደረጉትን የሰላም ጥረቶችን የሚያደናቅፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራዎች ናቸው በማለት የአብይ መንግስት አጥብቆ በመቃወም ላይ ይገኛል። እንዲሁም የቡድኑ ተከፋዮች ሕጎቹ እንዳይጸድቁ ጥረትና የተቃውሞ ሰልፎች እያደረጉ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ ፈላጊዎች ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።

904
0
Previous articleየኤስ 3199 ረቂቅ ህግ ፀደቀ
Next articleየመብት ጥሰቶችን በገልተኝነት ለማጣራት ለተሰየመው ቡድን የኢትዮጵያ መንግስት በጀት አልፈቅድም ማለቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወቀሰ።