Home ዜና መለስ ዜናዊን በጥቂቱ

መለስ ዜናዊን በጥቂቱ

1843
Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi addresses a press conference at his office in Addis Ababa on May 26, 2010. Ethiopian opposition groups rejected today the results of parliamentary elections which gave long-time ruler Meles Zenawi a landslide win, and demanded fresh polls. AFP PHOTO/SIMON MAINA (Photo credit should read SIMON MAINA/AFP via Getty Images)

“ሁልጊዜ ከእንቅልፌ የሚያባንነኝ ነገር ፍርሃት ነው፡፡ይህች ከ1ሺህ ዓመታት በፊት ታላቅ የነበረች ሃገር ባለፉት 1 ሺህ ዓመታት ወደ ታች ስታሽቆለቁል ቆይታለች፡፡በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ የሚራቡባትና የሚሞቱባት ህልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀባት ሃገር ነበረች፡፡የአሁኑ ፍርሃቴ የሃገሪቱ ህልውና አይደለም ፡፡ይህን አልፈነው ሄደናል፡፡ እኔን የሚያስፈራኝ ነገር አንድ ሰው የሆነ ቦታ ላይ በሚሰራው አደገኛ ስህተት ምክንያት አሁን በዚች ታላቅ አገር ውስጥ ፍንጩ መታየት የጀመረው የህዳሴ ጭላንጭል ተመልሶ እንዳይደበዝዝ ነው፡፡”

ይህ ንግግር አስረኛ የሙት ዓመታቸው ሰሞኑን የሚከበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነው፡፡ይህ ቃላቸው በመንግሥታዊው ዘመን መጽሔት ታትሞ ይገኛል፡፡


የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዚህ ንግግራቸው ከሃያ ዓመት በላይ ያስተዳደሯት አገር የሕልውና ሥጋት እንደሌለባት ጠቅሰዋል፡፡ይልቁንም ይህንን ሥጋት አልፈነዋል ይላሉ፡፡እንዲያም ሆኖ አሁን አገሪቱ የገጠማት የሕልውና ሥጋት መሆኑን ጠለቅ ብሎ ለሚያስብ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡እውነታው ይሄ ቢሆንም በርግጥ አቶ መለስ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለምን ደረሱ…አገሪቱ የመበታተን አደጋውን አልፈዋለች ሲሉ ምን ማለታቸው ነው የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ይሆናል፡፡

በርግጥ አቶ መለስ ኢትዮጵያን የሚበታትናት ድህነት መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩት ኖረዋል፡፡ምናልባትም በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መንግሥት የድህነት ፍልሚያ ውስጥ የገባበት ነው፡፡በሕዝቡም ውስጥ ለልማት ያለ በጎ አተያይና እንቅስቃሴ ተንፀባርቋል፡፡ምናልባት አቶ መለስ የመበታተን አደጋን ተሻግረነዋል ሲሉ፣ለመበታተን ምክንያት የሆነውን ጠላት (ድህነትን) ለመፋለም ቁርጠኝነት በማየታቸው ሊሆን ይችላል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ ከ17 ዓመታት የጎሬላ ትጥቅ ትግል በኋላ ሥልጣን ሲይዙ የተረከቡት አገር ምን ዓይነት ነበር የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ያስረከቡትንም አገር ሊያስታውሰን ይችላል፡፡እናም የሙት ዓመታቸውን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መለስ የተረከቧት ኢትዮጵያና ያስረከቧት ኢትዮጵያ እንዴት ያሉ ናቸው የሚለውን በጣም በትንሹ እንመልከት፡፡

ኢኮኖሚ

አቶ መለስ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አምስት መቶ ሺ ብር ያለው ኢትዮጵያዊ በዚች ሶስት ሺ ዓመት ኖርኩ በምትል አገር ውስጥ አልነበረም፡፡ረሃብ ከሚለው የኦክስፎርድ መዝገበ ቃል ፊት ለፊት ኢትዮጵያ የሚል ስምም የያዘች ነበረች፡፡እርሳቸው ሲሞቱ ግን በአፍሪቃ በርካታ ሚሊየነሮች ያሏት አገር፣በፍጥነት የሚያድግ ኢኮኖሚ በመገንባቷ የአፍሪቃ አንበሳ ተብላ የምትጠራ አገር፣በዘመናዊ ታሪኳ ረዥሙን የሠላም ዘመን የኖረች አገር፣ወዘተ በሚሉ ገለፃዎች የምትጠራ አገርን ለትውልድ ትተው አልፈዋል፡፡

ምናልባት መለስ ዜናዊና ባልደቦቻቸው ባይመጡ ኖሮ የዚች ኢትዮጵያ የተባለች አገር የኢኮኖሚና የወየበ ስም ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን በበጎ የመነሳት ዕድሉ ለተጨማሪ ዓመታት ይዘገይ እንደነበር የሚያነሱ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡መለስ የኢትዮጵያን ስም በሕዳሴ ለመመለስ የጣረ፣ለዚህም የተጋ መሪ ነው የሚለውን ሀቅ ክዶ የሚከራከር ተቺ ብዙም የላቸውም፡፡

መለስ ድህነትን የብሔራዊ ደህንነት ሥጋት፣የአገር አንድነት ፀርና የጋራ ሕልውና ተውሳክ አድርገው በመተንተን በእርሱም ላይ በመዝመታቸው ይመሰገናሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ መለስ ዜናዊ ለረዥም ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር የኖረውን ድህነትን አብራርተው፣በእርሱም ላይ ዘምተው ከተረከቡት አገር በብዙ እጥፍ የተሻለ አገር ለተተኪዎቻቸው ስለማስረከባቸው አሀዛዊ መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡አቶ መለስ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የአገሪቱ መሠረተ ልማትና ጥቅል አገራዊ ምርት ከእርሳቸው ሕልፈትም በኃላ ሆነ ከእርሳቸው ወደ ሥልጣን መምጣት በፊት አልታየም፡፡አቶ መለስ ድህነት የኢትዮጵያ ዋና ጠላት ነው ብለው ዘምተው አገራቸውን ከዚህ የብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ለመከላከል ቆላ ደጋ ብለው፣ከተማ ገጠር ተመላልሰው ሰርተዋል፡፡የተዋጣለት የዲፕሎማሲ ችሎታቸውንና የማሳመን ክህሎታቸውንም ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ እንዳዋሉት የእርሳቸውን ዘመን ኢትዮጵያ የተከታተሉ የዓለም ኢኮኖሚስቶች ይተርካሉ፡፡እርሳቸው ይህንን ከእንቅልፍ የመንቃት ጉዳይ ነው ይሉታል፡፡ በአንድ ወቅት የሚመሯትን አገር አሁናዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል ተብለው ሲጠየቁ ከረዥም ከፊል እንቅልፍ የነቃች በማለት መልሰው ነበር፡፡

በዚህም እርሳቸው ሥልጣን ሲይዙ የነበረው 300 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ወደ 4200 አሳድገው፣በሄክታር 10 ኩንታል ብቻ ይመረትበት የነበረውን የኢትዮጵያን ግብርና ወደ 23 ከፍ አድርገው፣የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት በብዙ እጥፍ ቀንሰው፣አማካይ የኑሮ ጣሪያን ከ45.5 ወደ 61.4 አሳድገው፣ከመቶ ሺህ ኪሎሜትሮች በላይ የአስፓልት መንገድ ገንብተው፣አንድም የዶላር ሚሊየነር ያልነበረባትን አገር እንደ ዘጋርዲያን (ዲሴምበር 4፣2013) እርሳቸው እስኪሞቱ ድረስ ሶስት ሺህ የሚደርሱ የዶላር ሚሊየነሮች ፈጥረው፣ በዓለም ባንክ መረጃ መቶ ዶላር አካባቢ የበረውን የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 500 ዶላር ከፍ አድርገው፣ስድስት ቢሊዮን የማይደርስ የነበረውን አጠቃላይ አገሪቱ ምርት ወደ ሰማኒያ ቢሊዮን ዶላር እንዲያድ ያደረገ መንግሥት መርተው፣ከዜሮ በታች ዕድገት የነበረውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከ10 በመቶ በላይ የሆነ ዓመታዊ እድገት እንዲኖረው ያስቻለ አመራር ሰጥተው፣በመቶ ዓመት የአገሪቱ ዘመናዊ የትምህርት ጉዞ ውስጥ ሁለት ብቻ የነበሩትን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እርሳቸው በ21 ዓመት ወደ 45 ለማሳደግ አመራር የሰጡና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን መቶ በመቶ ያሳካችን አገር  መርተው ያለፉ መሪ ነበሩ መለስ ዜናዊ!

ሉዓላዊነት

አቶ መለስ ግንቦት 1-1947 በትግራይ ክልል፣ በአድዋ ከተማ የተወለዱት የአድዋ ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ ከስድሳ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ በዚያች ሉዓላዊነትንና ክብርን ላለማስነካት ፍልሚያ በተደረገባት አድዋ የተወለዱት አቶ መለስ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በሥልጣን ዘመናቸው አብዝተው ስለመስራታቸው ታሪክ ሰንዶታል፡፡የወራሪ አገርን ሠራዊት ለመፋለም የዐገራቸውን ሀብትና ሰው አስተባብረው መርተዋል፡፡ በዚህም በባድመ ወረራና በአልሸባብ የጂሃድ ዕቅድ ላይ ወታደራዊ ድል አስመዝግበዋል፡፡ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመቀማት ያሰፈሰፉትን ኒዮሊብራል ሃይሎች በማለት በአደባባይ ተከራክረው አገራቸው ከዓለም ኢኮኖሚ ልታገኘው የሚገባትን ጥቅም ለማምጣት መታተራቸውና የአገራቸውን ስምና ዝናም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያደረጉበትን ገድል ዜና መዋዕላቸው ሰንዶታል፡፡

የኖቤል ተሸላሚው ጆሴፍ ስትግሊዝ ግሎባላይዜሽን ኤንድ ኢትስ ዲስኮንተንተንትስ በሚለው መጽሐፉ (ከገጽ 26-27) ይህንን የአቶ መለስን ፀረ-ኒዮሊብራሊስትነት አንስቶ ሲያብራራ ‹‹17 ዓመት በረሃ ለበረሃ የተንከራተትነው ለጋሽ አገሮችን አሳምነን ባገኘነው ገንዘብ አንድ ዓለማቀፍ ቢሮክራት ክሊኒንክና ትምህርት ቤት አትገነቡም ብሎ እንዲያዘን አይደለም›› በማለት ከአይኤምኤፍ ኃላፊዎች ጋር ሲከራከሩ እንዳደመጠ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአቶ መለስ ዘመን በርካታ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪቃ አገራት ቀዳሚ ሆና ነበር፡፡ይሁን እንጂ ይህም እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበትና የአገሪቱን የፖሊሲ ሉዓላዊነትና ነፃነት የማይጋፉ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚገቡ ነበሩ፡፡ ኬኒች ኦኖ learning to industrialize በሚለው መጽሐፉ (ገጽ 268) ይህንን ጉዳይ ሲያብራራው ‹‹ኢትዮጵያ ለጋሾች ከሚፈልጓቸው በርካታ የአፍሪቃ አገሮች በተለየ ሁኔታ እርዳታን በማጣጣም ወይም የበጀት ድጎማ በማድረግ ስም ወይም የብድር ቅድመ ሁኔታዎችን አትፈቅድም፡፡የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ ከባሕር ማዶ የሚመጣ እርዳታ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ከአገራዊ የልማት አቅጣጫዋ ጋር የተጣጣሙ ከሆነ ብቻ ነው›› ይላል፡፡

ይህ የአቶ መለስ ብሔራዊ አርበኝነትና ለሉዓላዊነት ያለ ቀናኢነት ያመጣው ነው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይሚኒስትር የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ ከሌሎች ነፃ እየወጡ ከነበሩ የዘመኑ አፍሪቃዊያን መሪዎች ጋር ሆነው የመሠረቱትን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ሕብረትነት እንዲቀየር ከማድረጋቸውም በላይ የሕብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የተደረገውን ጥረት ያከሸፉ ናቸው፡፡

በቶጎ ሎሚ በተካሄደው የሕብረቱ ስብሰባ ላይ የሕብረቱን ዋና መቀመጫ ከአዲስ አበባ ለማንሳት በሴኔጋሉ፣በግብጹና በሊቢያው መሪዎች የተነሳውን የተቀናጀ ሤራ ለማክሸፍ የተከተሉት ስልት የአቶ መለስን የተዋጣላት ዲፕሎማትነት ያሳየ ነበር፡፡ንግግራቸው የሚከተለው ነበር፡፡

‹‹የአፍሪቃ አንድነት መቀመጫን አዲስ አበባ እንዲሆን የወሰኑት እንደ ኒሬሬና ኒኩሩማሕ ያሉ ቀደምት መሪዎች ናቸው፡፡በወቅቱ አዲስ አበባ በአጼ ሃይለሥላሴ ሥር ነበረች፡፡በርግጥ ንጉሱ አሁን ካሉት የአፍሪቃ መሪዎች ጋራ በርዕዮተ ዓለም ሊነፃፀሩ አይችሉም፡፡ግን አንድ ሀቅ አለ፡፡ኢትዮጵያ በየትኛውም የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ሆና ለአፍሪቃ ነፃነት ጠንካራ አቋም ያላት ናት፡፡

ማንዴላን ያሰለጠናቸው ማነው፡፡አጼ ሃይለሥላሴ ናቸው፤ኢትዮጵያ ነች፡፡ሙጋቤ አገሩን ከቅኝ ገዥዎች ለማላቀቅ ሲታገል ከጎኑ የነበረው መንግሥቱ አይደለም እንዴ፡፡መንግሥቱ በአገር ውስጥ ጨፍጫፊ ነበር፡፡በአፍሪቃ ነፃነት ላይ ግን እርሱም እንደ ሀይለሥላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ላይ ያላት አመለካከት በመንግሥታት ለውጥ ውስጥ የቀጠለ ነው፡፡ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብቸኝነት ምን ያህል ከባድ እንደነበር ይረዳዋል፡፡በመንግሥታቱ ማሕበር ከአውሮፓውያን ጋር የገጠምነው ብቸችንን ነበር፡፡በወቅቱ የደረሰብንን አንዘነጋውም፡፡ዛሬ ግን ብቻችንን አይደለንም፡፡53 የአፍሪቃ አገራት ከገናችን አሉ፡፡የአንድነትን ትርጉም እናውቀዋለን፡፡ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ የዋለችው ውለታ የሴኔጋሉን ወዳጄን ያላረካ ከሆነ ጉዳዩን አፍረጥርጠን እንነጋገራለን፡፡

የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኔ ይገባኛል የሚል ካለ ይቅረብና በዝርዝር እንነጋገርበት፡፡ጉዳዩ ውስብስብ ነው፤ተጨማሪ ጥናትም ይፈልጋል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ለአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫነት ከኢትዮጵያ ይልቅ እኔ ይገባኛል የሚል ካለ ተጨባጭ ማስረጃና መከራከሪያ ያቅርብ››

መለስ የዲፕሎማሲውን መድረክ የአገራቸው ዋነኛ ጠላት አድርገው ለሰየሙት ድህነት መፋለሚያ የሚሆን ትጥቅ የሚገኝበት ለማድረግ ሰርተዋል፡፡እርዳታና ብድር እንዲገኝ፣የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ፣እንደ አጎዋ ያሉ ከታሪፍና ቀረጥ የነጹ የንግድ መድረኮች እንዲገኙ አድርገውበታል፡፡

መለስና ኢትዮጵያዊነት

አገር ማለት ሰው ነው የሚል መርህ የነበራቸው አቶ መለስ ዜናዊ፣ኢትዮጵያዊነት ለእርስዎ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው የመንደር ነፋስ የማያንገዳግደው የሚያኮራ ማንነት ሲሉ የመለሱት መልስ በርካቶች የሚያስታውሱት ነው፡፡ ‹‹የመንደር ነፋስ የማያናወጠው፣በጋራ ስንሆን የምንደመጥበት እውነት ነው›› ሲሉ ነበር የመለሱት፡፡

ኢትዮጵያዊነት ስሜት ሳይሆን ነባራዊ ዕውነታ ነው የሚሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይሚኒስትር ኢትዮጵያን እንደ አባይ ወንዝ ይወስዷትና ብሔር ብሔረሰቦቿን ደግሞ እንደ ገባር ይቆጥሯቸዋል፡፡ኢትዮጵያዊነት የነዚህ ገባሮች ድምር ውጤት መሆኑን አውስተው ኢትዮጵያ የሁሉም የሆነች በሁሉም ተሳትፎ እየሰፋች የሄደች፣አሁንም ሁሉም ሊያስቀጥላት የምትችልና የሚገባ ትልቅ ወንዝ ነች ይላሉ፡፡

አቶ መለስ የአገራቸውን የብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ድህነትን አድርገው በመነሳት፣ይህንን ጠላትና የደህንነት ሥጋት አድርገው ያስቀመጡትን አካል ለመፋለም ደግሞ በሁሉም መስክ የዘመቱ ናቸው፡፡የዲፕሎማሲውን መስክም ሆነ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴያቸውን ለዚሁ ዓላማ አውለውታል ከተባለ፣ኢትዮጵያዊነትንም በመንደር ነፋስ የማይናወጽ አለት አድርገው ከተመለከቱት አይቀር የአገር ፍቅር ስሜታቸውን እንዴት ይገልጹታል የሚለው ጥያቄ ሊመለስ ይገባዋል፡፡በየቀኑ በሚዲያ በመከሰት እዩኝ ተመልከቱኝ አዳምጡን አንብቡኝ የሚል ባሕርይ እንደሌላቸው የሚነገርላቸው አቶ መለስ በአንድ ወቅት ይቺን ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ለኔ አገር መውደድ ማለት ሕዝብን መውደድ ማለት ነው፡፡ለኔ አገር ማለት ሰው ነው፤ሕዝብ ነው፡፡ከዚያ ውጪ ተራራ ነው ወንዝ ነው፡፡አንድ ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ የበለጠ ፍቅር ሊያሳድር ይችላል፡፡አንድ ተራራ ከሌላ ተራራ የበለጠ ፍቅር የሚያሳድርበት ምክንያት ግን የለም›› ነበር ያሉት፡፡

‹‹አገር ማለት ሰው  ነው፡፡ለኔ አገር ማለት ተራራና ወንዝ ሳይሆን ሕዝብ ነው ሲሉም ከአድዋ ኮረብታዎች ይልቅ የአድዋ ነዋሪዎች፤ከወለጋ ጫካ ይልቅ የሆሮጉድሩ አርሶ አደር፣ከካራማራ ተራራ በላይ የጋራሙለታ አርብቶ አደር፣ከጉደር ወንዝ ይልቅ የጎንደር ነዋሪዎች ጉዳያቸው መሆኑን ለማስረዳት ነው፡፡የአገር ፍቅር አለኝ የሚል ሰውም በኢትዮጵያ ስም በመማልና በመገዘት ሳይሆን ከዋናው ጠላቱ ለማላቀቅ የሚከፍለው ዋጋ መመዘኛው ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

የአቶ መለስ ድክመት

አቶ መለስ በሥልጣን ዘመናቸው የአገሩን ኢኮኖሚ ለመለወጥ የሠሩትን ሥራ ያህል፣የዲፕሎማሲ ክህሎታቸውንና የመደራደር አቅማቸውን ተጠቅመው አገራቸውን ተደማጭና ተመራጭ የማድረጋቸውንም ያህል፣ የኢትዮጵያ መንግሥታት ጠላት ሆነው የኖረውን የኤርትራ መንግሥት በሕይወት እንዲቆይ ማድረጋቸው በዘመናቸው ከሚወቀሱባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ሻዕቢያ በአጼ ሃይለሥላሴ ዘመንም፣በመንግሥቱ ሃይለማርያም ዘመንም፣በእራሳቸው በአቶ መለስ ዘመንም ኢትዮጵያን ወግተዋል፡፡ከእርሳቸው ሞት በኋላም በአቶ ሃይለማርያም ዘመን በቀጥታና በውክልና ኢትዮጵያን ወግተዋል፡፡አሁን ደግሞ ከዘመናችን መሪዎች ጋር ሆነው ኢትዮጵያን የማፍረስ ውጊያውን ማካሄድ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው ወራት ቀርተዋል፡፡

ይህ የኤርትራ ጉዳይ የኢትዮጵያን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ሊጠናቀቅ የሚችልበት ወታደራዊ እድል በ1992 ዓ.ም የተገኘ ቢሆንም የያኔው የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መለስ ዜናዊ ወደ አስመራ እየገሰገሰ የነበረውን የኢትዮጵያ ጦር እንዲመለስ በማዘዝ የሻዕቢያ መንግሥት ተጠቅልሎ እንዳይወድቅና እንዲተርፍ ምክንያት የሆነ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገራት ሁሉ የላቀ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉልበት እንዲኖራት ያደረጉ ቢሆንም ይህ ጉልበታቸው ግን በትውልዶች መካከል የኢትዮጵያ ፀር ሆኖ ኖሯል የሚባልለትን ሻዕቢያን ለማስወገድ ሳያገለግል ኖሯል፡፡

ሌላኛው የአቶ መለስ የመሪነት ዘመን ችግር እርሳቸውም ሆኑ ጓዶቻቸው 17 ዓመታትን ለፈጀ የትጥቅ ትግል የተዳረጉበት፣አስርሺዎችም የተገበሩበት የዴሞክራሲ ጥያቄ በአግባቡና በሚገባው ልክ እንዲሰርጽ አለማስቻላቸው እንደሆነ ይነሳል፡፡ በርግጥ የሶስት ሺ ዓመት የመንግሥትነት ታሪክ አለኝ በምትለው በዚች አገር  ተቃዋሚዎች ፓርላማ ሲገቡ የታዩት፣መንግሥትን የሚወቅሱና ባለሥልጣናትን የሚዘልፉ ጋዜጦች የተነበቡት በአቶ መለስ ዜናዊ የሥልጣን ዘመን ነው፡፡ አቶ መለስ እያሉ በጠቅላላ አራት አገራዊ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን በመጀመሪያው የ1987ቱ ምርጫ 76 ተቃዋሚዎች ፓርላማ ገብተዋል፡፡ በ1992ቱ ምርጫ ደግሞ 66 የእርሳቸውና የመንግሥታቸው ተቃዋሚዎች የፓርላማ ወንበር አግኝተዋል፡፡በአወዛጋቢው የ1997ቱ ምርጫ ደግሞ በተቃዋሚነት የተመዘገቡ 174 ግለሰቦች ወደ ምክር ቤት ገብተው ከእርሳቸው ጋር ሲከራከሩ በቀጥታ ቴሌቭዥን ሲሰራጭ አምስት ዓመታት አልፈዋል፡፡ በአቶ መለስ ዘመን ዝቅተኛ የተቃዋሚ አሀዝ ወደ ፓርላማ የገባው በ2002ቱ ምርጫ ሲሆን ይህም ከአንድ በመቶ በታች ነበር፡፡

በዚህ መልኩ እየቀነሰ የመጣውን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ከ1997 ዓ.ም ወዲህ እያሽቆለቆለ የሄደውን የሚዲያ ነፃነት በማሻሻል ረገድ የራሳቸውን ሚና መወጣት የሚችሉበት ዕድል ቢኖርም ያንን ሳያደርጉት ሞት ቀድሟቸዋል፡፡ ብቁ ተተኪ አላፈሩም በሚልም የሚተቹት አቶ መለስ አሁን አገሪቱ የገባችበትን ምስቅልቅል ማስቀረት የሚችል የአመራር ሃይል መፍጠር ሳይችሉ መቅረታቸውን ያነሳሉ፡፡

የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ ከዚህ ዓለም ከተለዩ አስረኛ ዓመታቸው ሰሞኑን ይከበራል፡፡  

 በብርሃን ደረሰ ከባህርዳር