Home ዜና በአፋር ሰመራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በመድሀኒትና ምግብ እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች ለሞት...

በአፋር ሰመራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በመድሀኒትና ምግብ እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸው ተገለፀ፡፡

925

በአፋር ሰመራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በጊዜያዊ ማቆያው ውስጥ ከሚገኙት አብዛኞቹ ህፃናት የእድሜ ባለፀጎችና እናቶች  በተለያዩ በሽታዎች እየተጠቁ ለሞት እየተዳረጉ በመሆናቸው በተለያዩ የአለም ክፍሎች  የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እንዲደርሱላቸው ጠይቀዋል፡፡

ይህ በሜዳው የሚታየው የመቃብር ቦታ በሶርያ አልያም በሊቭያ አይደለም የኢትዮጵያ መሬት  እሾህ የሆነባቸው በመድሀኒት እጦትና በምግብ እጥረት ምክንያት በየቀኑ እንደ ቅጠል እየረገፉ ያሉት በአፋር ሰመራ ጊዜያዊ ማቆያ ተብሎ በየሜዳው ተጥለው ያሉ የትግራይ ተወላጆች እንጂ፡፡

እነዚህ በመድሀኒት እጦትና በምግብ እጥረት ህይወታቸውን ያጡት የትግራይ ተወላጆች  ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም በየጊዜው የአፋር ታጣቂዎች እየመጡ የፈለጉትን ትግራዋይ  በመውሰድ ወዳልታወቀ ስፍራ ወስደው መሰወር የተለመደ ሆኗል፡፡

በስምንት ወራት ውስጥ በሞት የተለዩ ወገኖች ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም አሁንም ግን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በየቀኑ እየሞቱ ከቀያቸው ውጭ በየሜዳው እየተቀበሩ ይገኛሉ፡፡ ትንሳኤ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሶ ባደረገው ዳሰሳ በእነዚህ ጥቂት ወራት የሞቱ ተጋሩ አጥንታቸው ያረፈበት ስፍራ አግኝቷል፡፡

ቀሪዎቹ በአፋር ሰመራ ጊዜያዊ ማቆያ በሜዳ ተጥለው የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች ደግሞ በረሀብና በሽታ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከዚያም አልፎ በማቆያው ውስጥ ያሉት ህፃናት ወላጆቻቸው የት እንዳሉ እንኳን እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት፤

ከስምንት ወራት በፊት በአብዓላ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በአፋር ታጣቂዎች ታፍሰው ወዳልታወቀ ቦታ ቆይተው ደግሞ ወደ ሰመራ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፤ ቁጥራቸው ወደ 15.000 የሚገመቱ የትግራይ ተወላጆች አብዛኞቹ ህፃናት የእድሜ ባለፀጎችና እናቶች ሆነው በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች የነበሩ ወጣቶችን እንደገደሏቸው ይታወቃል፡፡

በጊዝያዊ ማቆያው መድሀኒትም ሆነ በቂ ምግብ የለም፤ አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በመሆኑም አቅም የሌላቸው አረጋውያንና ህፃናት በቶሎ ለተለያዩ በሽታዎች እየተዳረጉ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ተቀምጠው የሚሞቱበትን ቀን መጠበቅ ሆኗል፡፡   

በአካባቢው ያሉት የትግራይ ተወላጆችም ካሉበት ችግር እንዲወጡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ድምፅ እንዲሆኑላቸውና በሚደረጉ እገዛዎች የቻሉትን ድጋፍ በማድረግ እንዲደርሱላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዊንታ ዘላለም