—-
ርሃብ፣ ስነልቦናዊ ጉዳቶች እና የጤና ደህንነት አለመኖር የመማር ማስተማር ሂደት ቀውሱ እንዳባባሱት እና መምህራን እና ተማሪዎች ልክ እንደ ተቀረው ህዝብ በርሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ዘግቧል፡፡
አለምአቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የትግራይ የትምህርት ስርዓቱን መልሶ በመገንባት ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ሲል ዘገባው አመላክቷል፡፡
በትግራይ የተማሪዎች የመማር ሂደት በጦርነቱ ምክንያት ተሰናክሏል በሚል ርእስ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ይዞት በወጣው ሰፊ ሐተታ በትግራይ ከሚገኙ 91 በመቶ በሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት 88 በመቶ የመማርያ ክፍሎች፣ 96 በመቶ ወንበሮች፣ 97 በመቶ ጥቁር ሰሌዳዎች፣ 85 በመቶ ኮምፒዩተሮች፣ 87 በመቶ ፕላዝማ ቴሌቭዥኖች በጦርነቱ መውደማቸውን የትግራይ ትምህርት ቢሮ መረጃን ዋቢ በማድረግ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ዘግቧል፡፡
ከቁሳዊ ጉዳቱ ባሻገር በጦርነቱ ከሁለት ሺህ አንድ መቶ አርባ በላይ የትምህርት ማሕበረሰብ አባላት መገደላቸውንና ከነዚህም 1911 ተማሪዎች ሲሆኑ 84 በመቶውም ሴቶች መሆናቸውን ከትግራይ ምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች ውጪ በስድስት ዞኖች ከጥቅምት ወር 2013 ዓ/ም እስከ መስከረም 2014 ዓ/ም ብቻ አካቶ የተካሄደው ጥናት ያመለክታል፡፡
የትግራይ የትምህርት ስርዓት በጦርነቱ ምክንያት በአስርት ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሷል የሚለው የኢትዮጵያን ኢንሳይት ዘገባ ልክ በ1980ዎቹ እንደነበረው የትግራይ ተማሪዎች አሁን ላይ በከባድ ብረት እና በመድፎች በፈራረሱ መማርያ ክፍሎች ላይ ገብተው ይማራሉ ከዚህ በፊት ይገለገሉባቸው የነበሩት ወንበሮች፣ ጥቁር ሰሌዳዎች፣ ኮምፒዩተሮች፣ ፕላዝማ ቴሌቭዥኖች እና ሌሎች የመማርያ መሳርያዎች አሁን ላይ የሉም ተዘርፈዋል አልያም ወድመዋል፡፡
በጦርነቱ እና ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት በትግራይ ወደ ትምህርት ገበታ የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ያመላከተው የዳሰሳ ጥናቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚልዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸውን ተገልጿል፡፡ ለዚህ ከፍተኛ የትምህርት ማቋረጥ አሃዝ ምክንያት ተብለው የተቀመጡትም ጦርነት፣ የቦንብ ድብደባ የፈጠረው የደህንነት ስጋት እንዲሁም የቀጠለው ከበባ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ የመማር ማስተማር ሂደት ባስቀጠሉ ትምህርት ቤቶች ላይ ለተማሪዎች እና ለአስተማሪዎቹ እጅግ የማይመች አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነባቸው የሚያትተው የኢትዮጵያ ኢንሳይት ዘገባ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ያለው አማካይ ርቀት በሶት እጥፍ ጨምሯል በ2013 ዓ/ም 2.5 ኪሎሜትር የነበረው አማካይ ርቀት በ2014 ዓ/ም ወደ 7.3 ኪሎሜትር ከፍ ማለቱን ተመላክቷል፡፡
ካለው የረሃብ አደጋ አንፃርም ተማሪዎች እነዚህን ኪሎሜትሮች በባዶ ሆድ ተጉዘው ትምህርት ቤት ለመድረስ ይገደዳሉ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የመምህራን ቁጥር መመናመንም አሳሳቢ ደረጃ የደረሰ ጉዳይ ነው ሲል ዘገባው አመላክቷል፡፡
በተከፈቱ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ከአንድ ዓመት በላይ ደመወዝ ባለመከፈላቸው አብዛኞቹ በቂ ምግብ የላቸውም በዚህም ህይወታቸውን አደጋ የሚጥል መከራ እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
መምህራን፣ አስተዳዳሪዎች፣ ወላጆች እና ተማሪዎች ስለ ህልውናቸው እና ስላልተረጋጋው ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አብዝተው ስለሚጨነቁ የትምህርት ስርዓቱ ግብ ላይ ትኩረት የማድረግ አቅም አጥተዋል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይት ዘገቧል፡፡
ርሃብ፣ ስነልቦናዊ ጉዳቶች እና የጤና ደህንነት አለመኖር የመማር ማስተማር ሂደት ቀውሱ እንዳባባሱት እና መምህራን እና ተማሪዎች ልክ እንደ ተቀረው ህዝብ በርሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንሳይት ሐተታ በማጠቃለያው በሶስት አራት አስርት ዓመታት ሂደት ውስጥ የተገነባው የትግራይ የትምህርት ስርዓት መልሶ ለመገንባት እና ህይወታቸውን ያጡ እና የተሰደዱ መምህራንን ለመተካት ብዙ ዓመታትን የሚፈጅ ቢሆንም ቁሳዊ ውድመቱ በአጭር ግዜ መልሶ ለመገንባት ከሰላም ሂደቱ ጎን ለጎን አለምአቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የትምህርት ስርዓቱን መልሶ በመንገባት ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ሲል ምክረ ሐሳቡን አስቀምጧል፡፡
ዳርይስማው ሃይሉ