Home ዜና የትግራይ አርሶ አደር በመጪው የክረምት ወራት የእርሻ ምርት ማምረት ካልቻለ በቀጣዩ ዓመት...

የትግራይ አርሶ አደር በመጪው የክረምት ወራት የእርሻ ምርት ማምረት ካልቻለ በቀጣዩ ዓመት የከፋ የርሃብ አደጋ   ተዘገበ፡፡

829

የትግራይ አርሶ አደር ለመጪው የመኸር ወቅት የሚሆን ምንም አይነት የእርሻ ግብአት እስካሁን እንዳላገኘና በመጪው ክረምት ምርት ማምረት ካልቻለ በቀጣይ አመት የከፋ የረሃብ አደጋ እንደሚያስከትል Ethiopia insite ዘገበ፡፡

የፋሽስቱ ቡድን ሰብአዊ እርዳታና የእርሻ ግብአት እንዳይገባ በትግራይ ህዝብ ላይ ያኖረው ክልከለና ከበባ ረሃብ እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት እንደሆነም ድረገጹ ዘግቧል፡፡

የትግራይ ጀኖሳይድ ጦርነት ባስከተለው ማህበራዊ ቀውስና ረሃብ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ትግራይ ውስጥ ህይወት ለመምራት ከባድ ነው፡፡ ምግብ የለም፤ የስልክ፣ የባንክ፣ የመብራት አገልግሎቶች እንዲሁም የገበያ ሰንሰለትና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የለም፡፡ በቀን አንዴም መብላት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምግብ ሳይበላ የሚውል ዜጋ ያለባት ትግራይ ብቻ ናት ይላል Ethiopia insite ድረገጽ ሐተታ፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መኖሩና በየቤታቸው በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ እና የሚሞቱ ህጻናት ቁጥር መበራከቱን ያተተው ድረ ገጹ ከበባውና ክልከላው ባለመነሳቱ በርሃብ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ  ህጻናት ህይወታችውን እያጡ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ታሪክ እንደሚመሰክረው ትግራይ በጦርነት ምክንያት ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ በሃይለስላሴና በደርግ ስርአት እንዲሁም በኢትዮ ኤርትራ እና በአሁኑ ጦርነት አስከፊ ጊዜያትን አሳልፋለች የሚለው ዘገባው በተለይ ባለፉት አምሳ አመታት ሶስት አስከፊ ጦርነቶች በማስተናገዷ ለተጨማሪ የርሃብ አደጋ ዳርጓታል፤ አሁን ደግሞ ለከፋ ሰው ሰራሽ ርሃብ ተጋልጣለች ይላል ዘገባው፡፡

በትግራይ ህዝብ ላይ ሆን ተብሎ ከበባና ክልከላ ማድረግ አሁን የተጀመረ አይደለም ያለው ዘገባው በሃይለስላሴ ዘመን የትግራይ ህዝብ በርሃብ እያለቀ እርዳታ እንዳይገባ ተከልክሎ እንደነበር ህዝቡ በርሃብ እየረገፈ ንጉሱ 80 አመታቸውን ለማክበር 35 ሚሊዮን ወጪ አድገዋል ሲል አስታውሷል፡፡

በደርግ ስርአትም ቢሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ዜጎች በርሃብ በሚያልቁበት ወቅት የደርግ ባለስልጣናት አደጋውን ከቁብ ሳይቆጥሩት 10ኛ አመቱን አክብሮ ነበር ያለው Ethiopia insite ዘገባ በ1977 ዓ/ም በርሃብና ድርቅ ሲሰቃይ የነበረው የትግራይ ህዝብ ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ሱዳን በሚሰደድበት ወቅትም በአምባገነኑ #ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ወደ ሱዳን እንዳይወጡ ከልክሏቸዋል፣ የአለም አቀፉ ተራድኦ ድርጅቶች የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲቃጠሉ አድርጓል ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ግፍ አትቷል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በትግራይ ህዝብ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከታወጀበት ግዜ ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር የትግራይ ህዝብ እንደተፈናቀለና፣ በተለይ የትግራይ አርሶ አደር ባለፉት ሁለት አመታት ምንም አይነት የእርሻ እንቅስቃሴ እንዳላደረገ የሚገልፀው፤  

የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ያፈራው ሃብት በፋሽስቱ ቡድን ቀጥረኛ ሰራዊት በአምባገነኑ የኢሳያስ ሰራዊትና በተስፋፊው የአማራ ሃይል ሆን ተበሎ መቃጠሉ፣ መዘረፉ እንዲሁም የቁም እንስሳት መታረዳቸውና መወሰዳቸውን ተከትሎ ህዝቡ ለከፋ የርሃብ አደጋ እንዲጋለጥ ማድረጉ ጠቁሟል፡፡

ከጦርነቱ በፊት በምርትና ምርታማነት መጨመር ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ እድገት የነበራት ትግራይ አሁን ወደ 1980ዎቹ ተመልሳለች ያለው ዘገባው ትግራይ ራሷን ችላ ምርታማነትን እንዳታሳድግ አርሶ አደሮች መዳበሪያና ምርጥ ዘርን ጨምሮ የእርሻ መሰረታዊ ግብአቶች የላቸውም፣ በመጪው ክረምት የእርሻ ስራ ካልተከናወነ ደግሞ በቀጣይ አመት አስከፊ ሊሆን ይችላል ሲል ስጋቱን አስቀምጧል፡፡

እንደርግ ስርአት ሁሉ የፋሽስቱ ቡድን ለመጪው ክረምት የሚጠቅሙ መሰረታዊ የእርሻ ግብአቶች ጨምሮ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ክልከላና ከበባ ማኖሩ አሁንም ርሃብ እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑን ያሳያል ነው ያለው፡፡

ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀሙ የትግራይ ህዝብ በረሃብና በሽታ ምክንያት ውድ  ህይወቱን እያጣ እንደሚገኝና የህዝቡ ኑሮና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ወደ 1980 መጀመሪያዎቹ እንደተመለሰ Ethiopia insite ዘገባው አትቷል፡፡

የአፈር መዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብአቶች እስካሁን ወደ ትግራይ አልደረሱም የሚለው Ethiopia insite ሐተታ ፣የእርሻ ግብአት መግባት የነበረበት አሁን ነው የትግራይ አርሶ አደር መጪው ክረምት ምርት ማምረት ካልቻለ ለቀጣይ አመት ከባድና ፈታኝ ይሆናል፣ አሁን ካለው የረሃብ አደጋ የከፋ ውጤት ይኖረዋል ብሏል፡፡

ከአለም ምግብ ፕሮግራም አገኘሁት ባለው መረጃ ድረገጹ እንደገለጸው 90 በመቶ የትግራይ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ አሁን ባለበት ሁኔታ መቀጠል ስለማይችል አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል፣ ከበባውና ክልከላው በአፋጣኝ መነሳትን በተመለከተ በትግራይ ህዝብ ዘንድ በቀዳሚነት ከሚጠበቁ የመፍትሄ እርምጃዎች አንዱ ነው ሲል Ethiopia insite ሐተታውን አጠቃሏል፡፡

ወ/ሚካኤል ገ/መድህን