የዶ/ር ቴድሮስ ብቸኛ ዕጩ ሆነው ዳግም መመረጣቸው የተረጋገጠው ጄኔቫ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው 75ኛው የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉብዔ ላይ ነው።ዶክተር ቴድሮስ ያለተፎካካሪ በብቸኛ ዕጩነት በቀረቡበት መድረክ ላይ ከተለያዩ የድርጅቱ አባል አገራት ለዕጩነት ለተሰጣቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የዓለም ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም በድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በእኔ ላይ ላላችሁ መተማመን እና ለጣላችሁብኝ እምነት አመሰግናለሁ” ብለዋል፤ ዶ/ር ቴድሮስ ተቋሙን በይፋ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሁለተኛ ዙር መምራት ይጀምራሉ።
ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት እአአ ከ2012 እስከ 2016 ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና መሠረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋታቸው እና የሕጻናት እና እናቶች ሞት መጠን መቀነሱ ይገለጻል ሲል BBC ዘግቧል።