በጦርነት ክፉኛ ወደ ተጎዳችው ትግራይ ክልል ህይወት አድን የህክምና መገልገያዎችን ለማድረስ የሚደረገው ጥረት የተገደበ መሆኑን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የትግራይ መንግስት ጊዚያዊ የተኩስ አቁም ቢያደርጉም የእርዳታ አቅርቦቱ ላይ መሻሻሎች እንደሌሉ ተቋሙ ገልጿል።
ከአምስት ወራት እግድ በኋላ ከጥር ወር ጀምሮ የህክምና ቁሳቀሶችን በአውሮፕላን በረራዎች እንዲያስገባ የተፈቀደለት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በየብስ እርዳታ ማስገባት እንዳልቻለ ለBBC አስረድቷል።
ቀይ መስቀል በባለፉት ሶስት ወራት በሰላሳ ስምንት በረራዎች አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ክልሉ ማድረስ ችሏል።
ነገር ግን በክልሉ ካለው መጠነ ሰፊ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር እየቀረበ ያለው “የውቅያኖስ ጠብታ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ቃለ-አቀባይ ፋጢማ ሳቶር ተናግረዋል።
በክልሉ ባጋጠመው የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ ዶክተሮች ጓንትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን እንደገና እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል ሲሉ ቃለ አቀባይዋ አስረድተዋል።