አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሃመር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለሚደረገው ጥረት ውጤታማ ስራ ይሰራሉ ተብሎ ተስፋ እንደተጣለባቸው አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእከተኛ በመሆን የተሾሙት እና በዲፕሎማሲው ሰፊ ልምድና አቅም እንዳላቸው የሚነገርላቸው አምባሳደር ማይክ ሃመር ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
France24 አሜሪካ በዲፕሎማሲ ስራ ልምድ ያላቸውና ትሁት የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሃመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልአክተኛዋን አድርጋ ሾመች ሲል ዘግቧል፡፡
ዴቪድ ሳተርፊልድ በመተካት አሁን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ሆኖው የተሾሙት ማይክ ሃመር ቀደም ብለው በቺሊ እንዲሁም በቅረቡ ደግሞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ዲፕሎማት ናቸው፡፡
እውነትን አፍረጥርጠው የሚናገሩ እና ተወዳጁ ዲፕሎማት ማይክ ሃመር ያላቸው አቅምና ልምድ ተጠቅመው #አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለምታደርገው ጥረት ውጤታማ ስራ ይሰራሉ ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶንዮ ቢሊንከን መግለጻቸውን በዘገባው ተመላክቷል፡፡
በተጨሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በማድረግ የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ፤ ሁሉን አካታች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖር አምባሳደር ማይክ ሃመር ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሩ መግለጻቸውን France24 አስነብቧል፡፡
አሜሪካ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስተኛውን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋን መሰየሟን የዘገበው BBC በበኩሉ ላለፉት አምስት ወራት ያህል በልዩ መልዕክተኝነት ቦታው ላይ የቆዩት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ኃላፊነታቸውን ለማስረከብ እየተዘጋጁ መሆናቸው ዘግቧል። የአዲሱ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር ሹመትም አሜሪካ ለአካባቢው ዲፕሎማሲያዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያላትን ቁርጠኝነት ያመለክታል ሲልም አክሏል፡፡
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሰየሙት መልዕክተኞች እነማን ነበሩ? ምን ጥረትስ አደረጉ? በሚል ሰፊ ሃተታ ይዞ የወጣው BBC አሜሪካ በሰሜን #ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከጥቂት ወራት በኋላ መጀመሪያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑትን በመላክ የጀመረችው ጥረት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስት አምባሳደሮች ተቀባብለውታል ብሏል።
መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ላይ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀን መልዕክተኛ ሆነው የተላኩት አምባሳደር ክሪስ ኩንስ የረጅም ጊዜ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ ኩንስ ኃላፊነቱን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአፍሪካ ቀንድ የልዩ መልዕክተኝነቱን ቦታ በዋናነት ይዞ የሚሰራ ሰው እስኪሰየም ድረስ ነበር ብሏል።
ኩንስ በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ቀውስ፣ ስለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በሱዳንና ኢትዯጵያ መካከከል ያለው የድንበር ውዝግብ በተመለከተ ከፋሽስቱ ቡድን አመራችና እና ከአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣንት ጋር ተገናኝተው ውይይት እንዳደረጉ የBBC ዘገባ አውስቷል።
ለአጭር ጊዜ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ሆነው የሰሩት ክሪስ ኩንስን በመተካት፣ አሜሪካ በኢትዮጵያና በአካባቢው ባሉ አገራት ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በቅርበት እንዲከታተሉ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ የሾመችው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለዘጠኝ ወራት የቆዩት ፌልትማን፣ የትግራይ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስለነበረው ተለዋዋጭ ሁኔታ፤ ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር አለመግባባት እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ውዝግብ የልዩ ልዑኩ ቀዳሚ ሥራ ነበሩ ያለው ዘገባው።
ተደጋጋሚ ጉዞ አድርገው ከፋሽስቱ ቡድን አመራሮች እንዲሁም ከትግራይ መንግስት ተወካዮች ጋር እንደተወያዩ ያስታወሰው BBC ይሁን እንጂ ፌልትማን እንደ ጥረታቸው በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በጠረጴዛ ዙሪያ ለንግግር እንዲቀመጡ በማድረግ ጦርነቱን የሚያስቆም ውጤት ማስገኘት አልተቻላቸውም ብሏል።
አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት በጥር ወር ላይ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን የተሰየሙት በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በመምጣት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከተባበሩት መንግሥት ኃላፊዎች እና ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገው ነበር።
ለአምስት ወራት ያህልም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እንደ ቀዳሚዎቻቸው ሁሉ በተልዕኳቸው ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያስገኙ ቦታቸውን ለአምባሳደር ማይክ ሐመር አስረክበዋል።
አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር በአፍሪካ ቀንድ አገራት ውስጥ ያለው ጦርነትና ፖለቲካዊ ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ማድረግ ዋነኛ ኃላፊነታቸው ይሆናል ተብሏል።
አምባሳደር ማይክ ሐመር ምን ይዘው እንደሚመጡ ባይታወቅም የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ የአሜሪካን ትኩረት ያገኘ መሆኑ እራሳቸውን ጨምሮ የቀደሙት መልዕክተኞች አሜሪካ ካሏት ዲፕሎማቶች መካከል አንቱ የተባሉትን ደጋግማ መሰየሟ ያመለክታል ሲል BBC ዘግቧል።
በወ/ሚካኤል ገ/መድህን