ጠላት የጀመረው የማጥቃት ዘመቻ አሁንም ሁሉንም አቅሙ ተጠቅሞ ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የትግራይ ሰራዊት መከላከያ መስመር ለመስበርና ትግራይና የትግራይን ህዝብ ለማበሳበስ የሚችለው ሁሉ በማድረግ ላይ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም፡፡
የትግራይ ህዝብ ኩራትና ደጀን የሆነው ጀግናው ሰራዊታችን ጠላት የጀመረውን የማጥቃት ዘመቻ በላቀ ፅናት በመመከት ምሽግህን ሳታስደፍር እያካሄድክው ያለውን ተአምራዊ ተጋድሎ ታሪካዊ ነው፡፡
ፊት ለፊትህ የገጠመህ የጠላት ሀይል የምታወቅው እና ደጋግመህ ያሸነፍከው ነው፡፡ ሰላምን ረግጦ የጀመረው ማጥቃት በአስተማማኝ መክተህ ለላቀ ተልእኮ ተዘጋጅ፡፡
ጠላት ላለፉት አምስት ወራት የሰላም ሃይል በመምሰል ዓለምን ለማደናገር ሲዋተት ቆይቷል፡፡ ለጦርነቱ ያስፈልጋል ያለው ሁሉ ዓይነት ዝግጅት እያደረገ ከቆየ ብኃላ ተፈጥራዊ ባህሪው የሆነውን በሃይል ፍላጎትና ህልሙን እውን ለማድረግ በደቡብ ግንባር ወረራ ጀምሯል፡፡
እንዲሁም በምእራብ ግንባር የማጥቃት ዘመቻ ለመጀመር እየተቀራረበ እንዳለ ባካሄድነው ጥብቅ ክትትል አረጋግጠናል፡፡ ጠላት ላለፉት ጥቂት ወራት ጊዝያዊ ግጭት በማቆም ወደ ሙሉ የሰላም ውይይት ለመግባት ሲደረግ የቆየው ጥረት ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ አድርጎታል፡፡ ይህ ፀረ ህዝብ የሆነው ስርዓት የሰላም መንገድን በመንፈግ በውስጡ ያለውን ሁለንተናዊ ቀውስ እና ያለ መረጋጋት በጦርነት ለመሸፈን ብሎ ወደ ባሰ እልቂትና ጥፋት የሚያስገባ ድርጊት እየፈፀመ ነው፡፡
ከጦርነትና ከግርግር ውጪ መኖር የማይችለው ይሄው የህዝብ ጠላት የሆነው ሃይል የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ መብቴ፤ ሰላም፤ ልማትና ዴሞክራሲ ብሎ ለጠየቀ ህዝብ እየጨፈጨፈ በየቀኑ የሰላማውያን ዜጎች ህይወት በከንቱ እንዲረግፍ እያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ፤ አፋር፤ ሶማሌ፤ ቤንሻንጉል፤ ጋምቤላ፤ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በአማራ ቁጥር ስፍር የሌለው የግፍ እልቂት እየፈፀመ ነው፡፡ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባው የጠላት ባህሪ ይሄው ነው፡፡እያደረገ ያለውም ይሄው ነው፡፡
የትግራይ ህዝብና መንግስት ለሰላም እና ድርድር ያለው ዝግጁነት ከመግለፅ አልፎ በተግባርም መደረግ የሚገባው ሁሉ ሲያደርጉ እና ሲጥሩ ቆይተዋል።
ይህ የምንናደርገው አመቺ ሁኔታ ላይ ሆነን ሳይሆን ሰለም የተመኘነው ለሰላም ብለን በህዝባችን ላይ ሊደርስ ከሚችለው ሁሉንም አይነት መከራ እና ስቃይ ተሸክምን፤ በርሃብ እና በበሽታ በየቀኑ ህይወት እየገበርን እና ለሰላም እጃችን ዘርግተን ቆይተናል።ከዛሬ ነገ መፍትሄ ይመጣል በሚል ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ችግር ተሸክመን በትግስት ስንጠብቅ ቆይተናል። አሁንም ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣው በሰላም እና በድርድር መሆኑ ዛሬም ይሁን የነገ የማያሻማ ፅኑ አቋማችን ነው። ቢሆንም ግን ሰላም እኛ ብቻ ስለፈለግነው እና ስለተመኘነው የሚመጣ አይደለም። ጠላት የሰላም መንገድ ጥሶ በጀመረው የሚቀጥል ከሆነ ለህልውናቸን እና ለዘላቂ ደህንነታችን ስንል እርምጃ ለመውሰድ እየተገደድን መሆኑን አለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲሁም የኢትዮጰያ ህዝቦች እና ሃይሎች ልትገነዘቡት ይገባል።
ህልውናችን እና ደህንነታችን በክንዳችን
ትግራይ ትስዕር
የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ ኮማንድ
ነሀሴ 18 2014
መቐለ