Home ዜና ዘንድሮ አለም-አቀፍ የኮምኒኬሽን ቀን እንደማመጥ በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና...

ዘንድሮ አለም-አቀፍ የኮምኒኬሽን ቀን እንደማመጥ በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና መከራ መደመጥ አለበት ተብሏል፡፡

897

ኮሚዩኒኬሽና መረጃ ለአንድ ማህበረ-ሰብ ብሎም ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡

የአለም የኮምኒኬሽንና መረጃ ፍሰት የበለጠ እንዲቃላጠፍ ብሎም የአለም ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ በእኩልነት እንዲረጋገጥ እንዲያስችል የአለም ኮምኒኬሽን ቀን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967 ጀምሮ በየአመቱ ግንቦት 17 ይከበራል፡፡ 

ዘንድሮ አለም አቀፍ የኮምኒኬሽን ቀን እንደማመጥ በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር ከኮምኒኬሽንና መረጃ ርቆ በጨለማ ውስጥ ያለው የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና መከራ መደመጥ አለበት ተብሏል፡፡

መረጃ ወይም መልእክት መስጠት አሊያም ማግኘት፣ ማሰተላለፍና ማሰራጨት እንዲሁም፣ ንግግርና ተግባቦት የኮምኒኬሽን ዘርፍ ቁልፍ ተግባራት ናቸው፡፡

የሰው ልጅ በበይነ መረብ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ወይም በመገናኛ ብዙሃን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ እና በአጠቃላይ መረጃ የማግኘት ወይም የመስጠት መብት እንዳለው በአለም አቀፍ ህግጋት ተደንግጓል፡፡

በሰለጠነው አለም በየትኛውም አቅጣጫ የሚከሰቱ አነጋጋሪ፣ አስደናቂና አሳዛኝ ድርጊቶች በዘመናዊ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሊጂ ውጤቶች በሰከንዶች ውስጥ ይሰራጫሉ፡፡ የአንድ ሃገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገትም በመረጃ ፍሰት ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

በያዘነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከሚባሉ መሰረታዊ ነገሮች መካከል መረጃ ወይም ኢንፎርሜሽን አንዱ ነው ተብሎ ይገለፃል ፡፡

ለዚህም ነው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1967 ጀምሮ አለም አቀፍ የኮምኒኬሽንና መረጃ ቀን በየአመቱ ግንቦት 17 ቀን እንዲከበር የተወሰነው፡፡ ዘንድሮም እንደማመጥ በሚል መሪ ሃሳብ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡

በዚሁ ጉዳይ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉ የትግራይ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል  ሃላፊ አቶ ሓዱሽ ካሱ እና ኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ኦፕሬሽን ጊዜያዊ አስተባበሪ አቶ ተስፋሁነይ ጉዕሽ መረጃ ለአንድ ማህበረ-ሰብ ወይም ህዝብ ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የላቀ ሚና እንዳለው ይናገራሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽ እና መረጃ የማግኘት መብትና ጥቅም በዚህ መልኩ ከተገለጸ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም የአለም ህዝብ በአለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉና መረጃ የማግኘት ወይም የመናገር የመሳሰሉ መብቶች ከተከለከለ 19 ወራት አልፈውታል፡፡

የትግራይ ህዝብ በፋሽስቶች ስልክና ኢንተርኔትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች የማግኘት መብቱን የተነፈገው በላዩ ላይ የደረሰበት እና እየደረሰበት ያለውን ግፍና መከራ በአለም አቀፍ ማህበረ-ሰብ እንዳይታወቅ ለመደበቅ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሓዱሽ ካሱ እና አቶ ተስፋሁነይ ጉዕሽ የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከመረጃ የራቀ በጨለማ ዘመን የሚኖር ከአለም የተገለለ ህዝብ ሆኗል ብለዋል፡፡

የአለም ማህበረ-ሰብ የኮምኒኬሽን ቀንን እንደማመጥ በሚል መሪ ሃሳብ ሲያከብር  በፋሽስቱ ቡድን እኩይ ሴራ እና ክልከላ ምክንያት ከአለም የተነጠለው የትግራይ ህዝብን ችግርና ሰቆቃ ማድመጥ አለበት ያሉት ሐሳብ ሰጪዎቹ የአለም ማህበረ-ሰብም የትግራይ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወ/ሚካኤል ገ/መድህን