Home ዜና የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አቀባበል ስነ ስርዓት

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አቀባበል ስነ ስርዓት

712

የዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ትግራይ ላይ በተካሄደው የጀኖሳይድ ጦርነት ላለፉት ሁለት አመታት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር ተማሪዎቹን እየተቀበለ ይገኛል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዛይድ ነጋሽ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዝርፍያና ውድመት ቢደርስበትም ባለው ግብአት ተጠቅመን ትምህርት ለማስጀመር ተማሪዎቻችን እየተቀበልን ነው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ቢሆንም የወደሙ መሰረተ ልማቶች ሁሉም እስኪሟሉ ድረስ መጠበቅ እንደሌለብን በማመን ባለዉ አቅም ትምህርት ለማስጀመር መወሰኑን የገለፁ ዶ/ር ዛይደ የፌዴራል መንግስትም የተዘረፈውና የወደመውን ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በትግራይ የመማር ማስተማር ሂደት እያስጀመርን ያለነው በቂ ግብአት ተሟልቶልን ሳይሆን የሰላም ስምምነቱ ተጠቅመን ያለውን እድል ወደ ጥቅም ለመቀየር በማሰብ ነው ያሉት ደግሞ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትህ ሽግግር እና ማህበራዊ ልማት ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሂወት ናቸው።

የተማረ የሰው ሃይል ማፍራት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፣ ስለሆነ ሁሉም ዘላቂነት ላለው ሰላም ሁላችን ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ያሉት ፕሮፌሰሩ በጦርነቱ የወደመች ትግራይ መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የአሁኑ ተማሪዎች ሃላፊነት የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የዓዲግራት ከተማ አስተዳደር የተጀመረው ሰላም እንዲቀጥል እና ዩንቨርስቲውን ለመደገፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርጉም አረጋግጠዋል።

ወ/ሚካኤል ገ/መድህን