Home ዜና የትግራይ መንግስትበመርህ ላይ የተመሠረተ የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ለመላክ...

የትግራይ መንግስትበመርህ ላይ የተመሠረተ የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

1615

የትግራይ መንግስት ተአማኒ ያልወገነ እንዲሁም በመርህ ላይ የተመሠረተ የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

የትግራይ መንግስት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ዛሬ እንዳስታወቁት በፕሬዝዳንት ኬንያታ አደራደሪነት በኬንያ ናይሮቢ እንደካሄድ በፓርቲዎች የተደረሰውን ስምምነት እንደግፋለን ብለዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ይህን ያስታወቁት ለሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር ማኪሳል፣ ለኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ጨምሮ ለተለያዩ ሃገራት፣ መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በላኩት ደብዳቤ ነው።

በዚሁ ግልፅ ደብዳቤያቸው የትግራይ መንግስት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከፋሽስቱ የአብይ ቡድንና ከሌሎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስለሚደረገው ውይይት የትግራይ መንግስት አቋም ግልፅ አድርገዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን በዚሁ ደብዳቤያቸው የጀኖሳይድ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥምቅት 2013 ዓ.ም ጀምሮ እና የትግራይ መንግስት  አብዛኛው የትግራይን አካባቢ ከተቆጣጠረበት ጊዜ  አንስቶ የትግራይ መንግስት በቅን-ልቦና የሰላም ድርድሩ በገለልተኛና ሶስተኛ ወገን እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ አስታውሰው ይህም ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መርሆዎች ጋር የሚጣጠም አቋም መሆኑን አመላክተዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

የአፍሪካ ህብረት በትግራይ ህዝብ ላይ በጀኖሳይድ ጦርነት የተፈፀሙ ግፎችን አስመልክቶ ዝምታ መምረጡ የአፍሪካ ህብረት የተመሠረተባቸው መርሆዎችን መካድ ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን በማያወላዳ መልኩ የአፍሪካ ህብረትና ልዩ መልእክተኛው አቋም የሚገባቸውን ሃላፊነት ያለመወጣታቸውና አቋም ያለመውሰዳቸው ከአፍሪካ ህብረት ድንጋጌ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት ፕሮቶኮል እንዲሁም ከሌሎች መርሆዎች አንፃር ሲቃኝ የሚፃረር አቋም በመሆን ስናወግዝ ቆይተናል ብለዋል።

ለሰላም ያለንን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ማሳየታችን መርሆዎቻችንን ወደ ጐን ገሸሽ ለማድረግ እንደተዘጋጀን ተደርጎ በስህተት እንዳይተረጐም ያሳሰቡት ዶ/ር ደብረፅዮን በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጐን ኦባሳንጆን ተቀብለን በክብር ማስተናገዳችን በአፍሪካ ሕብረት የእንግዳ አቀባበል መርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሁም ለአንድ የዕድሜ ባለፀጋ የሚገባን ክብር ከመግለፅ የመነጨ ነው ብለዋል ዶ/ር ደብረፅዮን።

ይሁንና የልዩ መልእክተኛው ከፋሸስቱ አብይ ያላቸውን ቅርበት ከህዝባችን የተሰወረ አይደለም ብለዋል ዶ/ር ደብረፅዮን በደብዳቤያቸው።

ዶ/ር ደብረፅዮን በደብዳቤያቸው የታንዛንያዋ ፕሬዝዳንት ሳምላ ስሉሁ ሓሰን የሰላም ጥረቱን ለመደገፍ ያሳዩት ዝግጁነት እንዲሁም የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና መንግስታቸው በመርህ ላይ የተመሰረተ ለማንም ያልወገነ  እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የሰላም ድርድር እንዲካሄድ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡