የትግራይ መንግስት ፕሬዚደንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር፣ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሀመርን እና ከሌሎች የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች በሰላማዊ ድርድሩና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
በተደረገው ውይይት ልኡካኑ የትግራይ መንግስት አቋም ምን እንደሆነ በሚድያ እንደሚነዛው ውዥንብር ሳይሆን በተጨባጭ የተረዱበት አጋጣሚ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የትግራይን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ዛሬ መቐለ የገቡት የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሀመር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ከትግራይ መንግስት ፕሬዚደንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ተወያይተዋል፡፡
ልኡካኑ በሰላም ሂደቱ ዙሪያ የትግራይ መንግስት አቋም ምን እንደሆነ በየሚድያው ከሚነዛው ውዥንብር ባለፈ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ የተረዱበት እንደነበር የትግራይ ሴንትራል ኮማንድ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡
የትግራይ መንግስትና ህዝብ አሁን እየገጠማቸው ያለውን የጀኖሳይድ ጦርነት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና እየተፈጸመ ያለ ችግር መሆኑን ለእንግዶቹ ገለጻ ተደርጓላችዋል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የሰላም ድርድሩ ሰላምን የሚያመጣ ከሆነ ረጅም ጊዜ ሳይወስድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እርምጃ መገባት እንዳለበት ዶክተር ደብረጽዮን ለልኡካኑ ገለጻ እንዳደረጉላቸውም ተናግረዋል፡፡
ልኡካኑ ከትግራይ መንግስት ጋር አራት ሰአታትን የወሰደ ውይይት ካደረጉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡
ይብራህ እምባየ