Home ዜና አሜሪካ ለኤርትራ ህዝብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዳትሰጥ በአምባገነኑ ኢሳያስ አገዛዝ መከልከልዋን አስታወቀች፡፡

አሜሪካ ለኤርትራ ህዝብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዳትሰጥ በአምባገነኑ ኢሳያስ አገዛዝ መከልከልዋን አስታወቀች፡፡

663
0

የአምባገነኑ የኤርትራ አገዛዝ በትግራይ የጀኖሳይድ ጦርነት እጁን በቀጥታ በማስገባት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙና ሩሲያ በዩክሬይን ላይ በከፈተችው ጦርነት ላይም ከሩሲያ ጎን መቆሙን ጤናማ ያልሆነ ወሳኔ ነው ሲሉ በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ስቲቨን ዎከር አውግዘዋል፡፡

በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ስቲቨን ዎከር ከውጭ ሃገር የሚሰራጨው የኤርትራ ሳተላይት ቴሌቪዥን ለሆነው ኤሪሳት እንዳሉት፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት/ USAID / ኤርትራ ውስጥ እንዳይሰራ በሃገሪቱ ባለሰልጣናት ከተከለከለ ከ2005 ወዲህ አሜሪካ የሰብአዊ ድጋፍ ለኤርትራ ህዝብ ማቅረብ አልቻለችም ብለዋል፡፡

የአምባገነኑ ኢሳያስ ባለስልጣናት እንከተለዋለን በሚሉት በራስ አቅም የመኖር መርህ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2006 በርካታ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ተቋማትን ከኤርትራ ማባረራቸው የኤምባሲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊ አስታውሰዋል፡፡

በአስመራ የሚገኝ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ውጪ ከሚገኙ የኤርትራ የሚድያ ተቋማት ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያ ነው ያለው የ BBC ዘገባ ከፍተኛ የስራ ኃላፊው ከቴሌቭዥን ጣብያው ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅን ተከትሎ  ነቀፌታ እንደደረሰባቸው የገለፁት ስቲቨን ዎከር  ለቃለመጠይቁ የወሰዱት ያልተለመደ ውሳኔ ግን አሜሪካ በኤርትራ ውስጥ የሚካሄደውን ተቋውሞ እንደምትደግፍ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል፡፡

አሜሪካ በኤርትራ ላይ የሚከተለውን የውጪ ፖሊሲ ለማብራራት በአምባገነኑ ኢሳያስ ቁጥጥር ስር ለሚገኙ የሚድያ ተቋማት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች አቅርበው እንደተከለከሉ ያስታወሱት ስቲቨን ዎከር አሁንም በማናቸውም ጊዜ ቢጠየቁ ከመንግስታዊ የሚድያ ተቋማት ጋር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2001 ጀምሮ አምባገነኑ ኢሳያስ በኤርትራ የፕሬስ ነጻነት መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ የሚድያ አዘጋጆችን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች እና የሚድያ ባለሙያዎች በስውር ቦታዎች ታስረው እንደሚገኙ አጋልጧል፡፡

የፕሬስ ነፃነት የጤናማ ዲሞክራሲያዊ እና የነጻ ሃገር የማእዝን ድንጋይ ነው ያሉት ስቲቨን ዎከር፣ የሰብአዊ መብት እና የኢኮኖሚ እድገት መሰረትም ነው ብለውታል፡፡

የኤርትራ ልማታዊ እንቅስቃሴ በሃገሪቱ በተዘረጋው ኢ-­­ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ምክንያት ተስተጓጉሏል፤ አገራዊ አገልግሎት በሚል ሰበብ በሃገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው የወጣቶች ነጻ ወታደራዊ አገልግሎት ግዳጅ ገደብ ሊበጅለት ይገባል በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምንም እንኳን የኤርትራ መጻኢ እድል በኤርትራ ህዝብ የሚወሰን ቢሆንም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በየማጎሪያ ስፍራዎች የሚገኙ የህሊና እስረኞች የሆኑ ኤርትራዊያን ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

የአምባገነኑ ኢሳያስ ቅጥረኛ ወታደሮች በትግራይ በታወጀው የጀኖሳይድ ጦርነት እጃቸውን በቀጥታ በማስገባት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል፤ በዚህም አሜሪካ  በአምባገነኑ ኢሳያስ አገዛዝ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ አስገዳጅ የኢኮኖሚ ማእቀብ እርምጃ መውሰዷን አስታውሰዋል፡፡

በመጨረሻም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ በመደገፍ ኤርትራ ከሩሲያ ጎን መቆሟን በማስታወስ ውሳኔው ጤናማ ያልሆነ ድርጊት በማለት በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊው ስቲቨን ዎከር ኮንኖውታል፡፡

አማረ ኢታይ

Previous article‘Escaping Eritrea’ የተሰኘ  በፍሮንትላይን የቀረበው ዶክመንታሪ ፊልም የፒቦድይ አዋርድ አሸናፊ ሆነ፡፡
Next articleበዓይደር ሆስፒታል በ12 ቀናት ውስጥ ብቻ በኦክስጅን አቅርቦትና  በመድሐኒት እጦት ምክንያት የ32 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተገለፀ፡፡