በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሃመር በጅቡቲ ፣ኳታርና ኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አሳውቋል።
አምባሳደር ማይክ ሃመር የሚያደርጉት ጉብኝት ከዛሬ ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከመንግስት አመራሮች ጋር ተገናኝተው ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም በተለይ ከትጥቅ መፍታትና የሰራዊት አባላት ከተሰናበቱ በኃላ መልሶ የማቋቋም ጉዳይ፣ የፍትህ ሽግግርና ተጠያቂነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ትኩረት በማድረግ ውይይት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳዮች ፅህፈት ቤቱ ባወጣው መግልጫ ግልፅ አድርጓል።
እንደ ፅህፈት ቤቱ ገለፃ አምባሳደሩ በጅቡቲም ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን በሚኖራቸው ቆይታም በሃገሪቱ በሚካሄድ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ተሳትፈው በሱዳን እየቀጠለ ያለውን አለመረጋጋት በመፍታት ረገድ ይወያያሉ ተብሏል።
#በታሪክ ፍሳሃ